ከተቀነባበረ የእንስሳት ምርት የወጪ ንግድ 128 ነጥብ 4 ሚሊየን ዶላር ገቢ ተገኘ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በ2018 በጀት ዓመት ከ24 ሺህ ቶን በላይ የተቀነባበረ የእንስሳት ምርት ወደ ውጭ በመላክ 128 ነጥብ 4 ሚሊየን ዶላር ተገኝቷል አለ የግብርና ሚኒስቴር።
የግብርና ሚኒስትር ዴዔታ ፍቅሩ ረጋሳ (ዶ/ር) እንዳሉት፥ በበጀት ዓመቱ 25 ነጥብ 9 ሺህ ቶን የተቀነባበረ የእንስሳት ምርት ለመላክ ታቅዶ 24 ነጥብ 2 ሺህ ቶን ተልኳል።
በዚህም 128 ነጥብ 4 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ገቢ መገኘቱን ተናግረዋል፡፡
በእንስሳት ልማት ላይ በተደረገ ትኩረት ተጨባጭ ውጤት እየተመዘገበ ቢሆንም ኢትዮጵያ ካላት የእንስሳት ሃብት አንፃር ውጤቱ አነስተኛ መሆኑን አስረድተዋል።
የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ሚኒስትር ዴዔታው ጥሪ አቅርበዋል።
የእንስሳት ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አስራት ጤራ (ዶ/ር) በበኩላቸው፥ በእንስሳት ምርቶች ወጪ ንግድ የተገኘውን ውጤት አጠናክሮ ለማስቀጠል አምራች ላኪዎች በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ አንስተዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ 2 ነጥብ 36 ሚሊየን የእርድ እንስሳት (ፍየልና በግ) ለኤክስፖርት ቄራዎች እንዲቀርብ ከባለድርሻ አካላት ጋር ለመስራት ታቅዶ 2 ነጥብ 4 ሚሊየን መቅረቡን ጠቅሰዋል።
በቀጣይ ከተቀነባበረ የእንስሳት ምርት ውጪ ንግድ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሰራም የሚኒስቴሩ የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ ይመር ዳውድ ለፋና ዲጂታል ገልጸዋል።
የእንስሳት ልማት ኢንስቲትዩት የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም እና 2019 ዕቅድ ላይ የፌደራና የክልል የስራ ኃላፊዎች እንዲሁም አምራች ላኪዎች በተገኙበት ውይይት መካሄዱን ጠቁመዋል።