ደቡብ ሱዳን በናይል ወንዝ ላይ የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ግድብ ልትገነባ ነው
አዲስ አበባ፣ መስከረም 11፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ደቡብ ሱዳን በናይል ወንዝ ላይ 1 ሺህ 800 ሜጋ ዋት ኃይል የሚያመነጭ የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ግድብ ለመገንባት ዝግጅት አጠናቅቃለች።
ግድቡ በደቡብ ሱዳን ምስራቅ ኢኳቶሪያ ግዛት ከኡጋንዳ ድንበር አቅራቢያ በምትገኘው ኒሙሌ ከተማ አቅራቢያ ባለው የፉላ ፏፏቴ የሚገነባ ሲሆን÷ የ”ፉላ ግድብ ፕሮጀክት” የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል።
የደቡብ ሱዳን ኢነርጂና ግድብ ሚኒስትር አጎክ ማኩር÷ ደቡብ ሱዳን እንደ ናይል ተፋሰስ ሀገርነቷ በወንዙ ላይ ግድብ የመገንባት ሙሉ የሉዓላዊነት መብት ያላት መሆኑን አረጋግጠዋል።
ደቡብ ሱዳን የተፈጥሮ ሀብቷን የማልማት መብት እንዳላት ጠቁመው ÷ በሃይድሮ ኤሌክትሪክ ግድብ ግንባታው ላይ ግብጽ ያሰማችው ተቃውሞ መሠረተ ቢስ ነው ሲሉ አጣጥለዋል።
ለአብነትም የፉላ ግድብ ፕሮጀክት ግብጽ በተካተተችበት የናይል ተፋሰስ ሀገራት የሚኒስትሮች ካውንስል እውቅና ማግኘቱን ተናግረዋል።
ግድቡ በናይል ተፋሰስ ሀገራት የሚኒስትሮች ካውንስል እውቅና ካገኙ 34 ፕሮጀክቶች እና ግድቦች አንዱ ነው ያሉት ሚኒስትሩ÷ ደቡብ ሱዳን የትኛውንም ጫና ወደ ጎን በመተው ግድቡን ትገነባለች ብለዋል።
የግድቡን የግንባታ ዝግጅት በተመለከተ ለሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ማያርዲት ሪፖርት ማድረጋቸውን እና በሚቀጥሉት ጊዜያት የግድቡ ግንባታ እንደሚጀመር አመላክተዋል።
የግድቡ ግንባታ 2 ቢሊየን ዶላር የሚገመት ወጪ የሚጠይቅ ሲሆን÷ በአሁኑ ወቅት የሀገሪቱ መንግሥት ዓለም አቀፍ ባለሃብቶችንና የገንዘብ ድጋፍ የሚያደርጉ ተቋማትን የማሳተፍ ሥራ እያከናወነ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።
ግድቡ ከተጠናቀቀ በኋላ የደቡብ ሱዳንን የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎት ከመሸፈን ባለፈ ጎረቤት ሀገራትን በኤሌክትሪክ ኃይል እንደሚያስተሳስር ታምኖበታል።
በሌላ በኩል ግብጽ በናይል ወንዝ ላይ በተለይም በቅርቡ የፍትሃዊ የውሃ አጠቃቀም የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ከጸደቀ በኋላ የሚገነቡ አዳዲስ ግድቦችን እንደ ስጋት ስትመለከት ቆይታለች።
በዚህም የደቡብ ሱዳን የፉላ ግድብ ፕሮጀክት ግንባታ ዕቅድ እየተቃወመች መሆኑን ስፑትኒክ እና የደቡብ ሱዳን መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
በሚኪያስ አየለ