Fana: At a Speed of Life!

ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ፍሬ … ተኪ ምርት

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሀገሪቱ ለበርካታ ዓመታት ስትከተለው የነበረውን መንግሥት በኢኮኖሚው ላይ ቀጥተኛ ቁጥጥር እና ጣልቃ የሚገባት ሞዴልን የቀየረ ነው፡፡
የኢኮኖሚ ማሻሻያው በዋናነት የግሉን ዘርፍ ማዕከል ያደረገ፤ ገበያ-መር ሥርዓት ለመገንባት የተነደፈ ታሪካዊ መዋቅራዊ የሪፎርም እርምጃ ነው።
የዚህ ታሪካዊ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ዋና ዓላማውም ባለፉት ዓመታት ያጋጠሟትን መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ፈተናዎች ለመፍታት እና የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ለማስቀረት፣ የዋጋ ንረትን እንዲሁም የሥራ አጥነት ችግርን በመቅረፍ ዘላቂ ብልጽግናን ማረጋገጥ ነው።
ማኑፋክቸሪንግ እና የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት የኢኮኖሚ የማሻሻያው ካተኮረባቸው ምሰሶዎች አንዱ ነው፡፡ በዚህ ዘርፍ የሀገር ውስጥ ምርቶችን ማበረታታት፣ የገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካት እና የግሉን ዘርፍ በኢንዱስትሪ ልማት ውስጥ በስፋት ማሳተፍ ላይ ትኩረት ያደረገ ነው ።
በዚህም ለሀገር በቀል ምርቶችና አምራች ኢንዱስትሪዎች ትኩረት በመስጠትና ድጋፍ በማድረግ ትልቅ አቅም በመፈጠር ላይ ይገኛል፡፡ ጥረቱም አመርቂ ውጤት እየታየበት ነው፡፡
አምራች ኢንዱስትሪዎችም በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች በመሰማራት በሚያመርቱት ተኪ ምርቶች ከሀገር ውስጥ ፍጆታ አልፎ ወደ ወጭ በመላክ የውጭ ምንዛሪ ገቢን ከፍ ያደርጋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም አምራቾች ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነታቸውን በማጎልበት እያገዛቸው ነው።
በዚህም ዘርፉ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመተካት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ በማስቀረትና አዳዲስ የሥራ ዕድሎችን በመፍጠር ሀገራዊ ኢኮኖሚውን በመቀየር ረገድ ጉልህ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።
በተከናወኑ ዐበይት የማሻሻያ ስራዎች አጠቃላይ የማኑፋክቸሪንግ አቅም ከነበረበት 47 በመቶ ወደ 67 በመቶ ሊደርስ ችሏል።
ከነባሮቹ የሐዋሳ፣ ኮምቦልቻ እና መቐለ የኢንዱስትሪ ፓርኮች በተጨማሪ በርካታ አዳዲስ ፓርኮች በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ተገንብተው ወደ ምርት ገብተዋ፡፡ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትም ወደ ዘርፉ እንዲገባ ተደርጓል።
በተሰሩ የማሻሻያ ስራዎች ጉልህ ውጤትች መታየት ጀምረዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል፤ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት የመተካት ዕቅዱ በተሳካ ሁኔታ ተግባራዊ እየተደረገ መጥቷል፡፡
እንደ ሲሚንቶ፣ ብረታ ብረትና ሴራሚክስ የመሳሰሉ የግንባታ ግብዓቶች በስፋት በሀገር ውስጥ መመረት በመጀመራቸው በሀገር ውስጥ ተኪ ምርቶች ብቻ በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር የውጭ ምንዛሪን ማዳን ተችሏል።
ዘርፉ ራሱን ከማሳደጉ ጎን ለጎን በርካታ አዳዲስ ጥቃቅን፣ መካከለኛ እንዲሁም ከፍተኛ አምራች ኢንዱስትሪዎችን በማፍራትና በማጠናከር ለዜጎች ሰፊ የሥራ ዕድል በመፍጠር በጥቅል ሀገራዊ ምርት ላይ አዎንታዊ ተፅዕኖን በማሳደር ላይ ይገኛል፡፡
በአጠቃላይ፣ ይህ ሀገር በቀል ማሻሻያ ለኢንደስትሪው ዘርፍ በሰጠው ትልቅ ትኩረት፣ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ምርቶች በሀገር ውስጥ ምርት በመተካት ኢኮኖሚው ላይ የነበረውን ጫና በማቅለል ላይ ይገኛል፡፡
ኢትዮጵያ በኢኮኖሚው ዘርፍ በምታከናውናቸው ማሻሻያዎች ከተረጂነት ወጥታ በራሷ ምርቶች የምትተማመን፣ የዓለም አቀፍ ኢንቨስትመንት ማዕከል እንድትሆንና የዜጎችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ዘላቂ ምጣኔ ሀብት እንድትገነባ በማድረግ ወደ ብልጽግና ጎዳና በመንደርደር ላይ ትገኛለች፡፡
በመልካም ፈቃዱ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.