Fana: At a Speed of Life!

10 አባላት ያሏቸው ቡድኖች በሚያጠናቅሩት ሪፖርት ላይ ከነገ ጀምሮ ምክክር ይደረጋል – ኮሚሽኑ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) አስር አባላት ያሏቸው ቡድኖች ሲያካሂዱት በነበረው ምክክር በተጠናቀሩ ሪፖርቶች ላይ ከነገ ጀምሮ ወደ 50 በመሰባሰብ ምክክር ይጀምራሉ አለ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን፡፡

ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርአያ (ፕ/ር) በዛሬው ዕለት በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፥ ምክክሩ አጀንዳዎችን በማብላላትና በምሁራን ገለጻዎች ተደግፎ በስኬት እየተካሄደ ይገኛል፡፡

ተመካካሪዎች በቡድን ተከፋፍለው የተሰጧቸውን አጀንዳዎች በትክክል በማብላላት፥ በመደማመጥና በመከባበር ወደ ሀሳብ ማጠናቀር ሂደት መሸጋገራቸውን አመልክተዋል።

በሂደቱ ተሳታፊዎች እርስ በእርስ እንዲቀራረቡና አጀንዳዎችን በጥራት እንዲያበላሉ በተዘረጋው አሰራር መሰረት ውጤታማ ስራ ተከናውኗል ነው ያሉት።

በሀገር ግንባታ፣ በታሪክ፣ በፌደራሊዝምና በማንነት ጉዳዮች ላይ በቂ እውቀትና ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች ለተሳታፊዎች ልዩ ግብአት የሚሆን ገለጻ ማቅረባቸውን ጠቅሰው፥ ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ መስጠታቸውንም ገልጸዋል።

ከነገ ጀምሮ አስር አባላት ያሏቸው ቡድኖች ሲያካሂዱት በነበረው ምክክር ያጠናቀሯቸውን ሪፖርቶች ወደ 50 በመሰባሰብ እንደሚያቀርቡና ምክክር እንደሚጀምሩ ተመላክቷል፡፡

በምክክር ጉባኤው 4 ሺህ ተሳታፊዎችን ማስተናገድ በርካታ ዝግጅቶችን የሚጠይቅ ቢሆንም የጤና፣ የጸጥታና ደህንነት እንዲሁም የትራንስፖርት ዘርፍ ተቋማት እያደረጉት ያለውን ቅንጅታዊ ድጋፍ አድንቀዋል፡፡

በዮናስ ጌትነት

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.