የነገዋን ኢትዮጵያ አብሳሪው ወደብ
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የመጨረሻዋ የዓመቱ ቀን ናት። ዛሬ ከምትጠልቀው ፀሐይ ጋር ዓመቱ ይሰናበታል።
ፀሐይዋ አዲስ ተስፋ ተሸክማ ነገ ትወለዳለች። ኢትዮጵያ ይህችን ቀን የነገ ብርሃን ማብሰሪያ አድርጋ ዛሬ ታስባታለች።
ብሩህ ነገ ግን ከሰማይ አይወርድም። በጠንካራ መሰረትና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ላይ ይገነባል።
ከአዲስ አበባ 73 ኪሎ ሜትር የሚርቀው የሞጆ ሎጂስቲክስ ማዕከል ይህንን አብሳሪ ነው። ይህ ስፍራ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ደም ስር ብቻ ሳይሆን፣ የነገዋ ዲጂታል ኢትዮጵያ ማሳያ ጭምር ነው።
ማዕከሉ ገና ከመግቢያ በር ጀምሮ ከቴክኖሎጂ ጋር በጥብቅ ተሳስሯል። ባለሶስት ደረጃ አውቶሜትድ የመግቢያ ስርዓት ተሽከርካሪዎችን በደቂቃዎች ውስጥ ወደ ኦፕሬሽን ይመራል።
በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገጠመው የሬይል ማውንትድ ጋንትሪ (RMG) ክሬን፣ ከ20 እስከ 40 ቶን መሸከም የሚችለው RTG ክሬን ጋር ተጋግዞ፣ እስከ ስድስት ኮንቴነሮችን ደራርቦ ይይዛል። ማዕከሉ ባለ 20 ጫማ አንድ ሚሊየን ኮንቴይነሮችን የመያዝ አቅም አለው።
ግዙፍ ክሬኖችን የገጠሙት ራሳቸው ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ናቸው፤ ይህም የቴክኖሎጂ ሽግግር ብቻ ሳይሆን የክህሎት ሽግግርም በር እንዲከፈትለት አድርጓል።
ከመግቢያ በር እስከ መጋዘን ድረስ ያለው እያንዳንዱ እንቅስቃሴ በደህንነት መቆጣጠሪያ ክፍል በሚገኝ ማዕከላዊ የመቆጣጠሪያ ቴክኖሎጂ ክትትል ስር ነው።
ዘመናዊው የሰርቨር ክፍል ደግሞ ከዚህ በፊት በተበታተነ መንገድ ይሰራ የነበረውን የሎጂስቲክስ ዘርፍ ወደ አንድ ወረቀት አልባ ዲጂታል ሥርዓት ቀይሮታል።
ይህ ማዕከል የራሱ የተለየ የኃይል አቅርቦትና የእሳት አደጋ መከላከያ ሥርዓት ስላለው፣ ስራው በምንም ሁኔታ ሳይስተጓጎል ይቀጥላል።
ይህ ሁሉ የሚያሳየው አንድ ነገር ነው። የነገዋ ኢትዮጵያ በጡብና በኮንክሪት ብቻ ሳይሆን፣ በዲጂታል መሰረተ ልማትም ጭምር እየተገነባች መሆኑን።
ይህ ቴክኖሎጂንና ዘመናዊነትን የታጠቀ ማዕከል ለነገዋ ኢትዮጵያ ሎጂስቲክ ብስራት ነው። የኢትዮጵያ ብልጽግና አይቀሬነትን ያበስራል።
ፀሐይ ዛሬ ትጠልቃለች፤ ነገ ግን በአዲስ ብርሃንና በአዲስ ቴክኖሎጂ ትወጣለች። የኢትዮጵያ ንግድ፣ ከጸሃይ መውጫ እስከ ጸሃይ መግቢያ ድረስ አይቆምም።
በአፈወርቅ እያዩ