የትግራይን ወጣት ለገበያ ያቀረበው ቆሞ ቀር
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በሰሜን ኢትዮጵያ የህግ ማስከበር ዘመቻ ወቅት የተካሄደውን ደም አፋሳሽ ጦርነት በሰላማዊ መንገድ ለመቋጨት የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ትልቅ ተስፋን ጭሮ እንደነበር ይታወቃል።
ነገር ግን የሰላም ተስፋው ፍሬ አፍርቶ የክልሉ ህዝብ ወደ መደበኛ ህይወቱ እንዳይመለስ እና ዘላቂ እፎይታን እንዳያገኝ እንቅፋት እየሆኑ ያሉ አካላት አሁንም ከእኩይ ተግባራቸው አልታቀቡም።
መርህ አልባነትን እና የትውልድን እልቂት እንደ ዋነኛ የፖለቲካ ማስፈጸሚያ ያደረገው ሕገወጡ የሕወሓት ቡድን፣ የትግራይን ህዝብ ለራሱ የስልጣን ማስንበቻ እንደ ቁሳቁስ በመጠቀም ለማያቋርጥ እንግልት እና ስቃይ ዳርጎታል።
ይህ ሕግና ስርዓትን የማያውቅ አጥፊ ስብስብ፣ የወጣቶችን አቅምና እድሜ በጦርነት አዙሪት ውስጥ ለማስቀጠል ጠብታ ርህራሄ የሌለው መሆኑን በተግባር እያሳየ ነው፡፡ የክልሉን ህዝብ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ህይወት በማፈራረስ፣ ትውልዱን ለጦርነት መመልመል እና ለጎረቤት ሀገራት እንደ ሸቀጥ ገበያ ማውጣት ዋነኛ ግብሩ ሆኗል።
የህዝብ ደህንነትና ሰላም ቅንጣት ያህል የማያሳስበው ይህ ቡድን ራሱን በስልጣን ለማክረም ሲል ከማንኛውም የጥፋት ኃይል ጋር ለመሰለፍ እና የሀገርን ህልውና የሚፈታተኑ ደላሎችን ጎትቶ ከማስገባት ወደኋላ አይልም። የኢትዮጵያን ሰላምና ልማት ከማይሹ ታሪካዊ ጠላቶቻችን ጋር በማበር ሉዓላዊነታችንን አደጋ ውስጥ ለመጣል እየተፍጨረጨረ ይገኛል፡፡
በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት የአረና ፓርቲ ሊቀመንበር አምዶም ገብረስላሴ እንደገለጹት፣ ቡድኑ በባህሪው የሰላም አየር መተንፈስ የማይችልና ችግሮችን በንግግር የመፍታት ባህል የሌለው ነው።
እንደ ፖለቲከኛው ገለጻ፣ ቡድኑ የፕሪቶሪያን የሰላም ስምምነት በግልጽ በመጣስ “ከእንግዲህ ጦርነት ይበቃናል” የሚል ጥብቅ አቋም እያንጸባረቁ የሚገኙትን የትግራይ ህዝብ፣ እናቶችና አባቶች እንዲሁም ወጣቶች በግዳጅ አፈሳ ወጣቶችን ወደ ማሰልጠኛዎች እያጎረ ይገኛል።
ይባስ ብሎም ከሀገር ውጭ ካሉ አሸባሪ እና ሕገወጥ ስብሰቦች ጋር በመሻረክ የትግራይን ወጣቶች የጥፋት መሳሪያ እያደረጋቸው እንደሆነ ጠቁመዋል።
ከዚህ በተጨማሪ የፕሪቶሪያውን ስምምነት ያፈራረሙ አካላትና ዓለም አቀፉ የዲፕሎማሲ ማህበረሰብ በቡድኑ ላይ አስፈላጊውን የዲፕሎማሲ ጫና እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
በተመሳሳይ የስምረት ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ምክትል ፕሬዚደንት ሀብቱ ኪሮስ በበኩላቸው፤ በአሁኑ ወቅት በትግራይ ክልል የሰብአዊ መብት ጥሰት እና ሕገወጥነት የሰፈነበት ሁኔታ መፈጠሩን አብራርተዋል።
ቡድኑ የራሱን የጫካ ሕግ በህዝቡ ላይ በመጫን የዜጎችን ክብርና ሉዓላዊነት ዝቅ በማድረግ ወጣቶች የራሳቸውን ታሪክ መስራት የሚችሉበትን እድል በማጨለም የጦርነት ነጋሪት እየጎሰመ ይገኛል ብለዋል።
የትግራይን ወጣት ልክ ገበያ እንደወጣ በሬ እየተደራደረ እየሸጠ መሆኑን አንስተው እናቶች ቀንና ሌሊት የሚያለቅሱበት፣ ወጣቶችም ከግዳጅ አፈሳ ለማምለጥ ሲሉ በየጫካውና የሚያድሩበት ከክልሉ የሚሰደዱበት አሰቃቂ ሁኔታ መፈጠሩን ተናግረዋል።
የትግራይ ህዝብ ከእንግዲህ ይህንን ከባድ የታሪክ እና የህሊና ሸክም የመሸከም አቅም የለውም፡፡ የትግራ ህዝብ ከኢትዮጵያዊያን ወንድም እህቶቹ እና ከሰላም ወዳዱ የዓለም ማህበረሰብ ጎን በመቆም ይህንን ሕገወጥ ስብስብ ከጫንቃው ላይ አውርዶ የመጣል ተጋድሎውን አጠናክሮ ይቀጥላል።
የሀገርን ሰላምና ህልውና ለማስከበር፣ የፕሪቶሪያው ስምምነት አስፈጻሚ አካላት እና መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በሰላም ዕጦት ውስጥ የሚገኘውን የትግራይ ህዝብ በመደገፍ የዚህን እኩይ ቡድን የመጨረሻ ውድቀት ማፋጠን ይገባል።
በዮናስ ጌትነት