በኦሮሚያ ክልል 58 መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ወደ ስራ ገብተዋል
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 18፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አወሉ አብዲ በክልሉ 58 መሶብ የአንድ ማአከል አገልግሎት መስጫ ማዕከላት ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ ነው አሉ፡፡
በክልሉ የመንግሥት አገልግሎት እና የአስተዳደር ሪፎርም ትግበራ በይፋ ተጀመሯል፡፡
አቶ አወሉ አብዲ በወቅቱ እንዳሉት፤ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ የክልሉ መንግሥት በሁሉም ዘርፎች ሪፎርም አድርጓል።
በሪፎርም ቅድሚያ ከተሰጣቸው መካከል የሰላም እና ደህንነት ጉዳዮች እንደሆኑ ጠቁመዋል።
የኢኮኖሚ ሪፎርምም በስፋት የተሰራበት መሆኑን አንስተው፤ በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በማዕድን፣ በቱሪዝም እና በአይሲቲ ዘርፎች በተደረጉ የኢኮኖሚ ሪፎርሞች ትላልቅ ለውጦች ተመዝግበዋል ነው ያሉት፡፡
መንግሥታዊ አስተዳደር እና አገልግሎት ዘመናዊ፣ ቀልጣፋ እና ጥራት ያለው እንዲሆን ለማድረግ ከታች ጀምሮ በየደረጃው ላለው መዋቅር ትኩረት መሰጠቱን ተናግረዋል።
በዚህም የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ተቋማትን ማደራጀት ላይ ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል።
በክልሉ እስካሁን በ96 ከተሞች መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ግንባታ መካሄዱን ገልጸው፤ ከነዚህ ውስጥ በ58ቱ አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን አመልክተዋል።
በሚልኪያስ አዱኛ