ባለፉት ዓመታት የሀገሪቱን ኢኮኖሚ የሚያጠናክሩ ስርነቀል ስራዎች ተሰርተዋል – ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ባለፉት ዓመታት የሀገሪቱን ኢኮኖሚ የሚያጠናክሩ ስርነቀል ስራዎች ተሰርተዋል አሉ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)፡፡
አቢሲኒያ ባንክ አ.ማ. በኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ መመዝገቡን ይፋ ማድረጊያ መርሐ ግብር ተካሂዷል፡፡
ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ የካፒታል ገበያን በማቋቋምና በማደራጀት ተጨባጭ ስራ መስራት ተችሏል።
እንደ ሀገር የካፒታል ገበያ አለመኖር ከፍተኛ ቁጭት ፈጥሮ መቆየቱን አስታውሰው፥ ይህንን ክፍተት ለመሙላት የካፒታል ገበያን በማቋቋም የተከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አመልክተዋል፡፡
አቢሲኒያ ባንክ ከካፒታል ገበያው ጋር ለመስራት ያሳየው ቁርጠኝነትና ውሳኔ የሚበረታታ ነው ብለዋል።
ይህም በኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ዕድገት ውስጥ ጠቃሚ ምዕራፍ በመሆን የገበያውን ተቋማዊ መሠረት የበለጠ እንደሚያጠናክረው ተመላክቷል፡፡
የግሉ ዘርፍ ተቋማት በሰነደ መዋዕለ ንዋይ ገበያው ውስጥ የሚያደርጉት ተሳትፎ እያደገ መምጣቱ የተገለጸ ሲሆን፥ ገበያውን መቀላቀል ለባለአክሲዮኖች እንዲሁም ለአጠቃላይ ኢኮኖሚው ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት ተጠቁሟል፡፡
የካፒታል ገበያው ለኢኮኖሚ ዕድገት፣ ለኢንቨስትመንት መስፋፋት እና የረጅም ጊዜ ካፒታል ማሰባሰብን በመደገፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ነው የተገለጸው፡፡
አቢሲኒያ ባንክ ከ980 በላይ ቅርንጫፎችን በመክፈት ሀገር አቀፍ የፋይናንስ ዘርፍ ተሳትፎውን አጠናክሮ መቀጠሉን ገልጿል፡፡
በሄኖክ ለሜ