የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ውጤት እያመጡ ነው
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት እያስመዘገቡ ካሉና ሰፊ የህዝብ ቁጥር ካላቸው ሀገራት መካከል ቀዳሚዋ ናት።
ሀገሪቱ የጀመረችውን ሁለንተናዊ የብልጽግና ጉዞ ለማፋጠን የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት የሚጫወተውን ሚና በመረዳት፣ መዋቅራዊና ስር ነቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን ስታደርግ ቆይታለች።
ቀደም ሲል ለውጭ ባለሀብቶች ዝግ የነበሩ የንግድ መስኮችን በመክፈት፣ መሠረተ ልማትን በማስፋፋትና የህግ ማዕቀፎችን በማሻሻል ረገድ የተደረጉት ጥረቶች ተጨባጭ ስኬቶችን እያስመዘገቡ ይገኛሉ።
የሀገሪቱ የኢንቨስትመንት ምኅዳር ማራኪ እንዲሆን የመደመር መንግሥት በርካታ ደፋር የፖሊሲ እርምጃዎችን ወስዷል፡፡
የገበያ ነፃነትና የውጭ ምንዛሬ ማሻሻያ ላይ በተሰራው ሥራ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ ተመን በገበያ እንዲወሰን በማድረጉ የባለሀብቶችን የትርፍ ክፍፍል ወደ ሀገራቸው የመመለስ ስጋት በከፍተኛ ደረጃ ቀርፏል።
ለረጅም ዓመታት ለሀገር ውስጥ ብቻ ተገድበው የነበሩት እንደ ባንክና ፋይናንስ፣ የጅምላና ችርቻሮ ንግድ፣ እንዲሁም የወጪና ገቢ ንግድ ዘርፎች በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት ተደርገዋል።
ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች እና የኢንዱስትሪ ፓርኮች ትኩረት ተሰጥቷቸው ተስፋፍተዋል፡፡
የኤሌክትሪክ ኃይል፣ መንገድና ቀልጣፋ የጉምሩክ አገልግሎቶችን በአንድ ማዕከል የሚያቀርቡ ዘመናዊ የኢንቨስትመንት ቀጣናዎች ተገንብተዋል።
ወደ ሀገር ውስጥ ለሚገቡ የካፒታል ዕቃዎች የጉምሩክ ቀረጥ ነፃ መብትና እንደየዘርፉ ከ4 እስከ 6 ዓመታት የሚቆይ የታክስ እረፍት ተሰጥቷል።
እነዚህ ሁለንተናዊ ጥረቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ የኢትዮጵያን ተወዳዳሪነት ያሳደጉ ሲሆን፣ ተጨባጭ የኢኮኖሚ ውጤቶችም ተመዝግበዋል፡፡
በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ዓመታዊ ሪፖርት መሠረት፣ ሀገሪቱ በ2025/26 በጀት ዓመት 4.32 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት በመሳብ የ8 በመቶ ዕድገት አሳይታለች።
ይህም ኢትዮጵያን በአፍሪካ ቀዳሚ የኢንቨስትመንት መዳረሻ አድርጓታል።
በዚሁ በጀት ዓመት ብቻ 528 አዳዲስ የኢንቨስትመንት ፈቃዶች የተሰጡ ሲሆን፣ ከ260 በላይ የሚሆኑት ፕሮጀክቶች በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ግንባታና ማምረት ተሸጋግረዋል።
የኤክስፖርት ዕድገት፡ በልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች ውስጥ የሚገኙ ኩባንያዎች ብቻ 225 ሚሊዮን ዶላር ዋጋ ያለው ምርት ወደ ውጭ በመላክ የ80 በመቶ ታሪካዊ ዕድገት አስመዝግበዋል።
ቻይና በ60 በመቶ የማኑፋክቸሪንግ ፕሮጀክቶች ቀዳሚ አልሚ ብትሆንም፣ እንደ ታደሽ ኃይል እና ጨርቃጨርቅ ባሉ ዘርፎች ከተባበሩት አረብ ኤምሬትስ፣ ሳዑዲ አረቢያና ቱርክ የሚመጡ ኢንቨስትመንቶች በከፍተኛ ሁኔታ ጨምረዋል።
በአጠቃላይ ኢትዮጵያ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ያደረገችው ጥረትና ያስመዘገበችው ስኬት የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን እያገዘ ይገኛል።
በመደመር መንግሥት የተወሰዱት ደፋር የፖሊሲ ማሻሻያዎችና የተገነቡት መሠረተ ልማቶች የዓለም አቀፉን የንግድ ማህበረሰብ እምነት መልሰው እንዲያንሰራራ አድርገዋል።