በአረንጓዴ ዐሻራ ተስፋን መትከል
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 22፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የኢትዮጵያን አጠቃላይ የደን ሽፋን ባለፉት ሰባት ዓመታት ውስጥ በተሰሩ ስራዎች ወደ 23 ነጥብ 6 በመቶ ከፍ ማድረግ ያስቻለና በየዓመቱ በተከወኑ መርሐ-ግብሮች ከ48 ቢሊየን በላይ ችግኞች የተተከሉበት ታላቅ ሀገራዊ ንቅናቄ ነው።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት በ2011 ዓ.ም የተጀመረው ይህ መርሐ ግብር፣ የአየር ንብረት ለውጥ ጫናን ለመቋቋም፣ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እና ለመጪው ትውልድ ስነ ምህዳሯ የተስተካከለ ሀገርን ለማውረስ የሚያስችል አያሌ ፋይዳ አለው፡፡
ቀደም ሲል ተራቁተው የነበሩ አካባቢዎችና መልክአ ምድሮች መልሰው በማገገማቸው፣ የአፈር መሸርሸር እንዲቀንስና የውሃ አካላት ዳግም እንዲያንሰራሩ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡
በዚህም የአፈር እርጥበትን በመጨመር የግብርና ምርታማነትን በማሳደግ ከፍተኛ ውጤት እያስመዘገበ ይገኛል፡፡
ችግኞችን ከመትከል ባለፈ ለእንክብካቤ ስራዎች በተሰጠው ከፍተኛ ትኩረት በሀገሪቱ በሁሉም አካባቢዎች የጽድቀት መጠን በአማካይ እስከ 82 በመቶ እና ከዚያ በላይ ከፍ እንዲል አድርጓል።
በመርሐ ግብሩ በመተከል ላይ ካሉ ችግኞች መካከል እንደ አቮካዶ፣ ማንጎ እና ፓፓያ ያሉ ተክሎች ላይ ትኩረት መደረጉ የማህበረሰቡን የምግብ ዋስትና እና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ከማሳደግ አንጻር አይነተኛ ሚና ይጫወታል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ለእንስሳት መኖነት የሚያገለግሉ የእጽዋት አይነቶች በስፋት በመተከላቸው በእንስሳት ምርት ላይ እድገት ተመዝግቧል።
በላይኛው የሀገሪቱ ተፋሰስ አካባቢዎች በተቀናጀ መልኩ በተከናወኑ የአፈርና ውሃ እንክብካቤ ስራዎች እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ያሉ ግዙፍ ግድቦችን ከደለል በመከላከል ብሎም የፍሰት መጠንን በማስተካከል ጋሻ በመሆን እያገለገለ ይገኛል፡፡
ኢትዮጵያ በሚሊየን የሚቆጠሩ ችግኞችን ለጎረቤት ሀገራት ማለትም ለጅቡቲ፣ ለሶማሊያ እና ለደቡብ ሱዳን በማድረስ የበረሃማነት መስፋፋትን ለመታደግ የሚደረገውን አፍሪካዊ ጥረት በግንባር ቀደምትነት በመምራትና ቀጣናዊ ትስስርን ለማጠናከር በመስራት ላይ ትገኛለች።
መርሐ-ግብሩ ሀገሪቱ የደን ሽፋንን በከፍተኛ ሁኔታ በማሳደግ የዓለም የአየር ንብረት መለዋወጥን ለመግታት በሚደረገው ትግል ውስጥ ግንባር ቀደም ስፍራ እንዲኖራት አድርጓል፡፡
በአረንጓዴ ዐሻራ እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን ይበልጥ በማጠናከር የመደመር መንግሥት በፈረንጆቹ እስከ 2030 ድረስ የሀገሪቱን ጠቅላላ የደን ሽፋን 30 በመቶ ለማድረስ አቅዶ እየሰራ ይገኛል፡፡
የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ተፈጥሮን ከማከም ባሻገር የትውልድን መጪ ጊዜ አረንጓዴ ካባን ያለበሰ፤ ለዜጎች ሰፊ የሥራ ዕድል የፈጠረ እና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እየተደረገ ያለውን ርብርብ ወደ ስኬት በማድረስ ላይ የሚገኝ ድንቅ ተግባር ነው።
የዘንድሮው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር “ተስፋን እንትከል” በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ ሲሆን፤ በዓመቱ የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ ንቅናቄ 800 ሚሊየን ችግኝ ሐምሌ 27 ቀን 2018 ዓ.ም ይካሄዳል።
በመልካም ፈቃዱ