አሜሪካ ኢትዮጵያ ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋት እያበረከተች ያለውን አስተዋፅኦ አደነቀች
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በአፍሪካ የአሜሪካ ዕዝ (አፍሪኮም) አዛዥ ጀነራል ዳግቪን አንደርሰን ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸውም በሁለቱ ሀገራት መካከል ባለው የመከላከያ ትብብር፣ በቀጣናዊ ደህንነት እና በጋራ የሚከናወኑ የወደፊት የትብብር መስኮች ላይ መክረዋል፡፡
ጀነራል ዳግቪን አንደርሰን ውይይቱን አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ እንዳሉት ÷ ከኢትዮጵያ ጋር ያለው የመከላከያ ትብብር በተለያዩ ዘርፎች እየተጠናከረ መጥቷል፡፡
ይህም በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የረጅም ጊዜ የመከላከያ አጋርነትና የጋራ ቁርጠኝነት የሚያንጸባርቅ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በውይይቱ የትብብር መስኮችን ማስፋት፣ በሶማሊያ አልሸባብንና አይኤስ አይኤስን ጨምሮ በሽብርተኝነት ላይ የሚደረገውን ትግል ማጠናከር እንዲሁም ወደፊት ያሉ የትብብር ዕድሎች መለየታቸውን አንስተዋል፡፡
ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋት ኢትዮጵያ እያበረከተች ያለችውን አስተዋፅኦ ያደነቁት ጀነራል መኮንኑ ÷ ከኢትዮጵያ ጋር በጋራ የአፍሪካ የሎጂስቲክስና የኮሙኒኬሽን ሲምፖዚዬምን ማዘጋጀት መቻላቸው በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው የመከላከያ ትብብር የደረሰበትን ከፍተኛ ደረጃ የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡
የሁለቱ ወዳጅ ሀገራት ግንኙነት ከጋራ ወታደራዊ ተልዕኮዎች ባሻገር ዘላቂና ዘመናዊ የመከላከያ አቅምን በመገንባት ላይ ያተኮረ ሲሆን÷ በአህጉሪቱ ያሉ የደህንነት ተግዳሮቶችን በጋራ ለመፍታት ያለውን ቁርጠኝነት እንደሚያሳይም ጠቁመዋል።
የአፍሪካ የሎጂስቲክስና የኮሙኒኬሽን ሲምፖዚዬም ልምድ ለመለዋወጥ፣ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ለማስተዋወቅ፣ ከንግድ ዘርፉ ጋር ትብብርን ለማሳደግና የአፍሪካ የመከላከያ ተቋማትን አቅም ለማጠናከር ያስችላል ነው ያሉት፡፡
በተጨማሪም ኢትዮጵያ የአህጉሪቱን ሀገራት በአንድ መድረክ በማሰባሰብ የጋራ የደህንነት ችግሮችን ለመፍታት ያላትን የአመራር ሚና እያሳየች መሆኑን ገልጸዋል።
የመከላከያ የውጭ ግንኙነትና ወታደራዊ ትብብር ዋና ዳይሬክትሬት ዳይሬክተር ሜጀር ጄኔራል ተሾመ ገመቹ በበኩላቸው÷ ውይይቱ ፍሬያማ እንደነበርና በኢትዮጵያና በአሜሪካ መካከል ያለውን የረጅም ጊዜ ወዳጅነትና የመከላከያ ትብብር የበለጠ የሚያጠናክር መሆኑን ተናግረዋል።
በውይይቱ ላይ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋን ጨምሮ የሁለቱ ሀገራት ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች መሳተፋቸውን የመከላከያ ኦንላይን ሚዲያ ለፋና ዲጂታል ገልጿል፡፡