ሃሳብን መሰረት ያደረገው የምክክሩ ስልታዊ ጉዞ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 22፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በተለያዩ ዘመናት የተከሰቱ የፖለቲካ አለመግባባቶች፣ የትጥቅ ግጭቶች እና የተሳሳቱ ትርክቶች ሲፈትኗት ቆይተዋል።
ይህንንም ተከትሎ የጋራ መፍትሔ ለማፈላለግ፣ መተማመንን ለመገንባት እና ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ሀገራዊ ምክክር እያከናወነች ትገኛለች፡፡
የምክክር ኮሚሽኑም ከአራት ዓመታት አድካሚ ዝግጅት በኋላ ሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ታሪካዊ የምክክር ጉባኤውን በአዲስ አበባ መጀመሩ ይታወሳል፡፡
የዚህ የምክክር ጉባኤ ልዩ ስነ ዘዴ እያንዳንዱ ዜጋና ተወካይ ያለምንም ፍርሃትና መገለል ሃሳቡ ሳይቀበር በነጻነት እንዲያቀርብ የሚያስችል እጅግ ጥንቁቅ አደረጃጀትን የተከተለ ነው።
በሂደት ላይ የሚገኘው የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ዛሬ የ250 ተመካካሪዎች የስልታዊ ቡድን ውይይት ጀምሯል።
የ250ዎቹ ስብስብ እነዚህን አጀንዳዎች በአንክሮ ያደምጣል፣ በስልታዊ እይታ ይመዝናል፣ በመጨረሻም የጋራ መግባቢያና መመሪያ እንዲሆኑ ተወያይቶ ያጸድቃቸዋል።
የ250ዎቹ ስልታዊ የቡድን ውይይት የተለያዩ እይታዎችን በሃሳብ ሚዛን ላይ አስቀምጦ፣ የጋራ መጻኢ ዕድልን በሰከነ መንፈስ ለመቅረጽ የሚደረግ ታላቅ የዲሞክራሲ ልምምድ ነው።
የዚህ ሀገራዊ ምክክር ዋናውና ትልቁ ጥንካሬ በሃሳብ ልውውጥና በጋራ ግንዛቤ ላይ ብቻ መመስረቱ ነው።
ሁሉም ነገር በጠረጴዛ ዙሪያ በሚደረግ መደማመጥ ላይ ብቻ የተንተራሰ መሆኑ የኮሚሽኑን ገለልተኝነትና የሂደቱን ታማኝነት ያሳያል።
አሁን እየተካሄደ ያለው የስልታዊ ቡድን ውይይት እንደተጠናቀቀ ምክክሩ በቀጣዩ ሳምንት 500 ተመካካሪዎችን ወደሚያሳትፈው ሰፊና ቀጣይ የምክክር ምዕራፍ ይሸጋገራል።
ይህም የኢትዮጵያ ህዝቦች በጋራ ጉዳዮቻቸው ላይ ለመወሰን እያደረጉት ያለው ጉዞ ተስፋ ሰጪ መሆኑን ያሳያል።
በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እየተከተለው ያለው ሳይንሳዊና ደረጃ በደረጃ የማሳደግ ስነ ዘዴ ሀገሪቱ ለዘመናት የተሸከመቻቸውን ውስብስብ ችግሮች በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ትልቅ መሰረት እየጣለ ይገኛል።
ችግሮችን በውይይት በጠረጴዛ ዙሪያ መፍታት ኢትዮጵያ ወደ አዲስና አስተማማኝ የጋራ ተስፋ ምዕራፍ እየተሻገረች መሆኑን የሚያበስር ታሪካዊ ስኬት ነው።
በሶስና አለማየሁ