በ3 ሺህ ድሮኖች የደመቀው የዋዜማ ምሽት፡ በራስ አቅም ወደ ቴክኖሎጂ ከፍታ
ዘመኑ የቴክኖሎጂ እና የፈጠራ ውድድር የገነነበት ነው። ሀገራት ከሰለጠነ የሰው ኃይል ባለቤትነት እስከ ዲጂታል ሽግግር አዳዲስ ከፍታዎችን ለመቆናጠጥ በእሽቅድድም ላይ ናቸው፡፡
በዚህ ዓለም አቀፍ ነባራዊ ሁኔታ ውስጥ ኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በመደመር መንግሥት እሳቤ በቴክኖሎጂው መስክ እያመጣች ያለችው ለውጥ እና እያስመዘገበችው ያለው ድል አበረታች ነው፡፡
በተለይም በራስ አቅም እና በሀገር ውስጥ ባለሙያዎች ታግዞ በአዲስ ዓመት ዋዜማ የተካሄደው ግዙፉ የ3 ሺህ ድሮኖች ትርዒት የዚህ ሰፊ የቴክኖሎጂ ጉዞ ማሳያ ነው፡፡
በዋዜማው የተከናወነው አስደናቂ ሁነት የውጭ ባለሙያዎችን እና ቴክኖሎጂዎችን ብቻ ጥገኝነት በመከተል የተደረገ ሳይሆን ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በትምህርት፣ በሳይንስና በፈጠራ ዘርፍ ማልማት የቻለችውን የሰው ኃይል ብቃት መጠቀሟን በግልጽ ያሳየ ትልቅ ምዕራፍ ነው።
ወጣት ኢትዮጵያውያን መሐንዲሶች እና ባለሙያዎች የድሮኖቹን የበረራ ስልተ ቀመር፣ የቁጥጥር ሥርዓት እና ሌሎች አሰራሮችን በራሳቸው እውቀትና ትጋት ማቀናጀት ችለዋል።
ይህ ስኬታማ የድሮን ትርዒት ሀገሪቱ ለቴክኖሎጂ ዘርፍ የሰጠችው ትኩረት ፍሬ ማፍራት መጀመሩን ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያውያን ለታላላቅ የዲጂታል ፈጠራዎች ዝግጁ መሆናቸውን ጭምር የሚያሳይ ነው፡፡
ይህ የሰው ኃይል ልማት ከዘመኑ ቴክኖሎጂ ጋር ተጣጥሞ መጓዙ ሀገሪቱ በቴክኖሎጂው ዓለም ያላትን ሉዓላዊነትና በራስ መተማመን ከፍ አድርጎታል።
የአዲስ ዓመት መባቻን በማስመልከት በአዲስ አበባ ሰማይ ላይ የተከናወነው ይህ የ3 ሺህ ድሮኖች ትርዒት የከተማዋን ሌሊት ውብና ማራኪ ከማድረጉ ባለፈ አዲስ ዓመትን አብሳሪ መልዕክቶች የተላለፉበት ነበር፡፡
ድሮኖቹ በአንድነት በመቀናጀት በሰማይ ላይ የፈጠሯቸው የተለያዩ ባህላዊ፣ ታሪካዊ እና አዳዲስ ሀገራዊ መልዕክቶችን አዘል ቅርጾች ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂ ዘርፍ አስደናቂ እመርታ እያሳየች መሆኑን የሚያረጋግጡ ናቸው፡፡
ይህ ትርዒት የኪነ ጥበብ እና የሳይንስ ውህደት ምን ያህል ማራኪ ሊሆን እንደሚችል ያሳየ፣ የኢትዮጵያን አዲስ ብሩህ ተስፋ እና የዕድገት ጎዳና በሰማይ ላይ በደማቅ ብርሃን የጻፈ ነው።
በርካታ ነዋሪዎች እና እንግዶች በአንድነት በመሆን የአዲስ ዓመትን ፅንሰ ሀሳብ ከቴክኖሎጂ ከፍታ ጋር አገናዝበው ተመልክተውበታል።
በራስ አቅም የተከናወነው ይህ የድሮን ትርዒት የአንድ ምሽት ድምቀት ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ ምን ያህል ርቀት መጓዙን የሚያሳይ ቋሚ ምስክር ነው።
የኢኮኖሚው ዋና ማዕቀፍ እየሆነ የመጣው ቴክኖሎጂ እንደ ግብርና፣ ጤና፣ ቱሪዝም እና ደህንነት ባሉ መሰረታዊ ዘርፎችም የሀገር ውስጥ አቅምን በመጠቀም ዘላቂ መፍትሄዎችን ለማምጣት ትልቅ መነሳሳትን ይፈጥራል።
በአዲስ ዓመት ዋዜማ የታየው ይህ ስኬት ኢትዮጵያ ችግሮቿን በራሷ አቅም እየፈታች፣ በዓለም አቀፍ ደረጃም ተወዳዳሪና አዲስ ታሪክ መጻፍ የሚችሉ ልጆቿን ይዛ ወደ አዲስ የዕድገት ምዕራፍ እየተሸጋገረች መሆኗን ያረጋግጣል፡፡
የነገዋ ኢትዮጵያ የቴክኖሎጂ ከፍታ ከዚህም በላይ የላቀ እንደሚሆን እና ሌሎች በዘርፉ እየተከናወኑ የሚገኙ ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውንም አመላካች ነው፡፡
በመላኩ ገድፍ