Fana: At a Speed of Life!

ከለውጡ በፊት የአማራ ክልል ከልማት አንጻር የሚገባውን ያህል ተጠቃሚ አልነበረም – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 25፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ከለውጡ በፊት የአማራ ክልል ከልማት አንጻር የሚገባውን ያህል ተጠቃሚ አልነበረም አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ከአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) ጋር በወቅታዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ቆይታ አድርገዋል።
በቆይታቸውም በለውጡ ማግስት ከህዝብ ጋር በነበረኝ ቆይታና ውይይት የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት አንዱ አንኳር ጥያቄ ነበር ብለዋል፡፡
የአማራ ክልል ከልማት አንጻር የሚገባውን ያህል ተጠቃሚ አልነበረም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ይህ ችግር የአማራ ክልል ችግር ብቻ አይደለም፤ በኢትዮጵያ ደረጃም ማደግ ባለብን ልክ ዕድገት አልተረጋገጠም ሲሉም ገልጸዋል፡፡
ነገር ግን ባለፉት ጥቂት ዓመታት ችግሩም እያለ የሄድንበት ርቀት ቀላል የሚባል አይደለም ነው ያሉት፡፡
ከመስኖ አንጻር መገጭ 18 ዓመት መቆየቱን ገልጸው፤ ከፍተኛ የመጠጥ ውሃ ችግር ጎንደር ላይ መኖሩን አስረድተዋል፡፡
በአማራ ክልል ያሉ ግድቦችን ለማጠናቀቅ ብዙ ቢሊየን ብር ወጥቶባቸው የማይናቅ ስራ መሰራቱን አብራርተዋል፡፡
በግብርና ዘርፍ በለውጡ ማግስት አማራ ክልል በዓመት የሚያመርተው 90 ሚሊየን ኩንታል ገደማ ብቻ እንደነበር አመልክተዋል፡፡
ግድቦች ላይ፣ ማሽነሪዎች ላይ፣ ማዳበሪያ ላይ፣ ሰፋፊ ስራ መሰራቱን ጠቁመው፤ ፓምፕ በስፋት ማስገባት በመቻላችን ባለፉት ዓመታት የአማራ ክልል ዓመታዊ ምርት ከዕጥፍ በላይ አድጓል ብለዋል፡፡
በኢንደስትሪ ዘርፍ ባህርዳር ኢንደስትሪያል፣ ደብረብርሃን፣ አረርቲ ኢንደስትሪያል ፓርክ፣ የጣና በለስ ስኳር ፋብሪካ ከለውጡ በኋላ ነው የተጠናቀቁት ሲሉም ገልጸዋል፡፡
ለሚ ሲሚንቶ ፋብሪካ የግለሰብም ቢሆን መንግስት ከፍተኛ ድጋፍ አድርጎለት ከለውጡ በኋላ መሰራቱን ጠቁመዋል፡፡
ዘይት ፋብሪካዎችን ጨምሮ የተለያዩ ፋብሪካዎች በስፋት በአማራ ክልል በባህርዳር፣ በጎንደር፣ ኮምቦልቻ እና ደብረ ብርሃን ተሰርተዋል ነው ያሉት፡፡
በዘርፉ ብዙ እመርታ መምጣቱን ጠቅሰው፤ በፊት ከነበረበት ሊወዳደር እንደማይችልና በብዙ እጥፍ ዕድገት ማሳየቱን ገልጸዋል፡፡
በቁጥር፣ በመጠን እና በስራ ዕድል ፈጠራ የተሰሩት ስራዎች ከለውጡ በፊት ከነበረው ጊዜ ጋር ለውድድር የሚቀርብ አይደለም ብለዋል፡፡
በቴዎድሮስ ሳህለ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.