አረንጓዴ ዐሻራ የተፋሰስ ጥበቃን በማጠናከር የግድቦችን ደኅንነትና የውሃ ምንጮችን እያጎለበተ ነው
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) አረንጓዴ ዐሻራ የተፋሰስ ጥበቃን በማጠናከር የግድቦችን ደኅንነትና የውሃ ምንጮችን እያጎለበተ ነው አሉ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር)።
ሚኒስትሩ እንዳሉት፥ ባለፉት ዓመታት በአረንጓዴ ዐሻራ የተተከሉ ችግኞች በብዙ መንገዶች የኢትዮጵያውያንን ሕይወት እየቀየሩ ነው።
መርሐ ግብሩ የፈጠረው የኢኮኖሚ ዕድልም የአትክልትና ፍራፍሬ የግብርና ምርታማነትን በማሳደግ ለወጪ ንግድ ዕድገት ጉልህ ሚና እየተጫወተ ይገኛል ነው ያሉት።
የመሬት መሸርሸር አደጋን ከመከላከል ባሻገር ውሃ ወደ ከርሰ ምድር እንዲሰርግ በማድረግ የተፈጥሮ ምንጮች፣ ጉድጓዶችና ወንዞች የውሀ መጠን እንዲጨምር እያገዘ ነው ብለዋል።
በተጨማሪም የአፈር መሸርሸርን በመቀነስ፣ የአፈር ለምነትን በመጠበቅና የተፋሰስ ሥነ ምህዳርን በማጠናከር የደረቁ ምንጮች እንደገና እንዲያገግሙ ማስቻሉን ተናግረዋል።
ይሀም በዓባይ፣ አዋሽና ሌሎች የኢትዮጵያ ወንዞች ተፋሰስ በተደረጉ ጥናቶች መረጋገጡን አመልክተዋል፡፡
ደርቀውና ጠፍተው የነበሩ የውሃ ምንጮችን በመመለስና በዝናብ ወቅት የሚከሰትን የጎርፍ አደጋ በመቀነስ ለአፈርና ውሃ ጥበቃ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል ነው ያሉት፡፡
የሐሮማያ ሐይቅ መመለስም በኢትዮጵያ የሥነ ምህዳር ጥበቃና የተፋሰስ ልማት ታሪክ ውስጥ ከተመዘገቡ ትልልቅ ስኬቶች መካከል አንዱ መሆኑን ጠቁመዋል።
አረንጓዴ ዐሻራ የተፋሰስ ጥበቃን በማጠናከር የግድቦችን ደኅንነትና የውሃ ምንጮች እየጠበቀ ይገኛል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡