Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ ያሰበችውን ሳታሳካ ጀምበር አትጠልቅም – የዓለም መገናኛ ብዙሀን ምስክርነት

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በስኬት ያጠናቀቀችው የአንድ ጀምበር የ800 ሚሊየን ችግኞች መርሐ ግብር ዓለምን ማስደመሙን ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሀን እየዘገቡ ይገኛሉ፡፡

ሚሊየኖች የተሳተፉበትን ይህን ሀገራዊ መርሐ ግብር ከዘገቡ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን መካከል ሮይተርስ፣ የቻይናው የዜና ወኪል ሽንዋ እና ኤፒኤ ይገኙበታል፡፡

ሮይተርስ በዘገባው በመርሐ ግብሩ ላይ ከ26 ሚሊየን በላይ ዜጎች በነቂስ በመውጣት መሳተፋቸውን በመግለጽ፥ በአንድ ጀምበር 800 ሚሊየን ችግኞችን የመትከል ዕቅዱን ለማሳካት ኢትዮጵያውያን ያደረጉትን ርብርብ አድንቋል፡፡

በዚህ ዓመት በአጠቃላይ ከ8 ቢሊየን በላይ ችግኞች እንደሚተከሉ የጠቆመው ዘገባው፥ እስካሁን 6 ነጥብ 5 ቢሊየን ችግኞች መተከላቸውንና በቀጣይም ተጨማሪ 1 ነጥብ 5 ቢሊየን ችግኞች እንደሚተከሉ አመላክቷል፡፡

የቻይናው የዜና ወኪል ሽንዋ በተመሳሳይ ኢትዮጵያውያን በአንድ ጀምበር 800 ሚሊየን ችግኞችን የመትከል ዕቅዱን ያሳኩበትን አንድነት በአድናቆት አንስቷል፡፡

መርሐ ግብሩ በፈረንጆቹ 2019 በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት መጀመሩን ያስታወሰው ዘገባው፥ አሁን ላይ በኢትዮጵያ በሁሉም አከባቢዎች በዘመቻ መልኩ እየተከናወነ መሆኑ አብራርቷል፡፡

የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብሩ የውጭ ሀገር ዜጎችን ጭምር ለተሳትፎ የጋበዘ አንድነት የታየበት እንደነበር ነው ሽንዋ ያስነበበው፡፡

መርሐ ግብሩን በእንጦጦ አካባቢ በመገኘት መከታተሉን የጠቀሰው የዜና ወኪሉ፤ የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ ዐሻራ በዓለም ላይ በአረንጓዴ ልማት ዘርፍ ከተከናወኑና ትኩረትን ከሳቡ የንቅናቄ ስራዎች አንዱ መሆኑን ጠቅሷል፡፡

ሌላኛው የዜና ምንጭ ኦል አፍሪካ ባወጣው ዘገባ፥ መርሐ ግብሩ የመሬት መራቆትን በመከላከልና የደን ሽፋንን በመጨመር ለአየር ንብረት ተጽዕኖ የማይበገር ከባቢን ለመፍጠር ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው አስነብቧል፡፡

አረንጓዴ ዐሻራ በኢትዮጵያ አስተማማኝና ዘላቂ ለማትን ለማረጋገጥ ለሚደረገው ጥረት መሰረት የሚጥል መሆኑን አመላክቷል፡፡

ኤፒኤ፣ ቲቪ ብሪክስ፣ ኢስላማድ ፖስት፣ ዘ ስታር፣ ሆርን ዲፕሎማት፣ ኤፍ ኤክስ ቢዝነስ፣ ሜድ አፍሪካ፣ ቻርማር ኒውስን ጨምሮ በርካታ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዘሃን ለአንድ ጀምበር የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ሰፊ ሽፋን ሰጥተዋል፡፡

በሚኪያስ አየለ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.