የወላይታ የባህል፣ የታሪክና ቋንቋ ሲምፖዚየም በወላይታ ሶዶ ከተማ እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ፣ መስከረም 9፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የወላይታ ብሔር የባህል፣ የታሪክና ቋንቋ ሲምፖዚየም በወላይታ ሶዶ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።
“ባጭራ ቄራ” የተሰኘው የወላይታ ብሔር የዘመን መለወጫ በዓል ‘ጊፋታ’ የዋዜማ ስነስርዓት “የትውልድን ቅርስ እንጠብቅ፤ የጊፋታን ውርስ እናስቀጥል” በሚል መሪ ሀሳብ በተለያዩ ዝግጅቶች እየተካሄደ ነው።
በዓሉን አስመልክቶ በተዘጋጀው ሲምፖዚየም ላይ የብሔሩን ቋንቋና ባህል የሚመለከት ውይይት የሚደረግ ሲሆን፣ የቱሪስት መዳረሻ በሆነው የዳሞታ ተራራ ጉብኝት ይካሄዳል፡፡
ጊፋታ በዩኔስኮ ከተመዘገበ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ በሚከበረው የዘንድሮው በዓል ላይ “ጊፋታ በዩኔስኮ” እንዲሁም ሌሎች መጽሐፍት እንደሚመረቁ ነው የተገለጸው።
ሲምፖዚሙ የብሔሩን ባህል፣ ታሪክና እሴቶችን ጠንቅቆ የሚያውቅ ትውልድ ለመፍጠር ያለመ ነው፡፡
በሲምፖዚየሙ ላይ የፌዴራል፣ የክልልና የዞኑ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እየተሳተፉ ይገኛሉ።
በማቴዎስ ፈለቀ