Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ የውሃ ሃብትን በፍትሃዊነት የመጠቀም አቋምና የግብጽ መሰረተ ቢስ ውንጀላ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ግብጽ ኢትዮጵያ የውሃ ሃብቷን የመጠቀም መብቷን በመጣስ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እና በአባይ ወንዝ የውኃ አጠቃቀም ዙሪያ አሁንም መሰረተ ቢስ ክሶችን እያቀረበች ትገኛለች፡፡

ግብጽ የዓባይን ወንዝ በብቸኝነት ለመቆጣጠር እና የሌሎችን ሀገራት የልማት መብት ለመቃወም የሚያስችላት ምንም አይነት ሕጋዊ መብት የላትም።

ከ85 በመቶ በላይ የሚሆነው የዓባይ ወንዝ ውሃ ከኢትዮጵያ የሚመነጭ ቢሆንም ግብጽ ከታሪካዊ ቅኝ ግዛት ስምምነቶች በመነሳት ብቻ በዓባይ ወንዝ ትልቅ ድርሻ እንዳላት በሀሰት ትርክት እያዋዛች ስትገልጽ ቆይታለች፡፡

ለዚህም ታላቁ ሕዳሴ ግድብ እንዳይገነባ ፤ግንባታ ከጀመረ በኋላም በፍጥነት እንዳይጠናቀቅ በርካታ ሴራዎችን ስትጎነጉን እንደነበር ይታወቃል፡፡

ይሁን እንጂ በኢትዮጵያውያን የጋራ ሀብት እና የጋራ ጥረት ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከተጠናቀቀ በኋላ ግብጽ የሴራ ስልቷን በመቀየር ግድቡ ስጋት ደቅኖብኛል ስትል ተደጋጋሚ ክሶችን ታቀርባለች፡፡

ከሰሞኑ ደግሞ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በግድቦቼ ላይ ያለውን የውሃ መጠን እንዲቀንስ አድርጎብኛል በማለት ኢትዮጵያን በሀሰት እየወነጀለች ትገኛለች፡፡

አህራም ኦንላይን የግብጽ ውሃ ሀብትና መስኖ ሚኒስቴር የዓባይ ወንዝ ውሃ ዘርፍ ም/ኃላፊ የሆኑትን ሳሜህ አብዱል ራህማንን ጠቅሶ እንደዘገበው ÷ ግብጽ በግድቡ ላይ የሚከናወነውን የውሃ ፍሰትና የተርባይን ሥራ በቅርበት እየተከታተለች መሆኑን አመልክቷል፡፡

ኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በተገቢው መልኩ እያስተዳደረች አይደለም በሚል በሀሰት የሚከሰው ዘገባው÷ ኢትዮጵያን ወደ አስገዳጅ ድርድር ማምጣት ለግብጽ ደህንነት ብቸኛ መፍትሔ መሆኑን አስቀምጧል፡፡

እነዚህ እና በግብጽ መገናኛ ብዙሃን የሚነዙ መሰረተ ቢስ ውንጀላዎች ካይሮ ኢትዮጵያ የውሃ ሀብቷን እንዳትጠቀም እና እንዳታድግ ካላት ጥልቅ ፍላጎት የሚመነጭ እንጂ ሕዳሴ ግድብ የደቀነባት አንዳች የደህንነት ስጋት ኖሮ አይደለም፡፡

ከ85 በመቶ በላይ የሚሆነው የዓባይ ወንዝ ባለቤት የሆነችው እና በፍትሃዊ ተጠቃሚነት መርሕ የምታምነው ኢትዮጵያ በታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት የውሃ እጥረት እንዲከሰት ምንም አይነት ፍላጎት የላትም፡፡

የአባይ ገባር ወንዞች ያላቸው የውሃ መጠን እንዳይቀንስም ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ዐሻራና ሌሎች ሥራዎች ለናይል ወንዝ የምታበረክተው የውሃ መጠን ለመጨመር በቁርጠኝነት እየሰራች መሆኑን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ገልጿል፡፡

ያም ሆኖ ግብጽ በአስዋን ግድብ እና ናስር ሐይቅ  እንዲሁም በከርሰ ምድር ከፍተኛ መጠን ያለው የውሃ ክምችት እንዳላት መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

ግብጽ በዓባይ ወንዝ ባላት የቅኝ ግዛት ዘመን አስተሳሰብ በውሃ ሃብት ዘርፍ ትብብርን እና ዲፕሎማሲን ከመምረጥ ይልቅ ኢትዮጵያን የማፍረስ እና የማግለል የከሸፈ እና የተሳሳተ ፖሊሲ እየተከተለች ትገኛለች፡፡

ላለፉት አስርት ዓመታት ኢትዮጵያ እና የናይል ተፋሰስ ሀገራት በዓለም አቀፍ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች የሕግ ማዕቀፍ ከግብጽ ጋር በትብብር ለመስራት ቢሞክሩም ካይሮ ግን በዓባይ ወንዝ የጋራ ተጠቃሚነት መርሕ ለመስማማት ፈቃደኛ ሳትሆን ቀርታለች፡፡

ኢትዮጵያ ከ85 በመቶ በላይ የሚሆነውን የውሃ አስተዋጽኦ የሚያበረክተውን የዓባይ ወንዝ ያለአንዳች ጉዳት በፍትሃዊና በጋራ ተጠቃሚነት መርሕ መጠቀም እንደሚገባ ታምናለች።

በአንጻሩ ሉዓላዊነቷን ለመዳፈር እና የተፈጥሮ ኃብቷን የማልማት መብቷን ለመንጠቅ ለሚሞክሩ አካላት ምንጊዜም ቦታ የላትም፡፡

በሚኪያስ አየለ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.