የሕዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ በትብብር መስራት ይገባል – አፈ ጉባዔ አብዱልሰላም
አዲስ አበባ፣ መስከረም 18፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ዛሬ የተረከብነው የሕዝብ አደራ በቁርጠኝነትና በታማኝነት ማገልገልን የሚጠይቅ ነው አሉ የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባዔ አብዱልሰላም ዋሪዎ።
የጨፌ ኦሮሚያ 7ኛ የሥራ ዘመን የ2019 ዓመት የመጀመሪያ ጉባዔ እየተካሄደ ነው።
በጨፌው የመጀመሪያ ጉባዔ አፈ ጉባዔ ሆነው የተመረጡት አቶ አብዱልሰላም ባስተላለፉት መልዕክት÷ ዛሬ የተረከብነው የሕዝብ አደራ በቁርጠኝነትና በታማኝነት ማገልገልን የሚጠይቅ ነው ብለዋል።
ሰላምን ለማስከበር፣ የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ፣ አዋጆችንና ደንቦችን ለመተግበር፣ ወጣቶችንና ሴቶችን በማሳተፍ የሕዝቡን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት ጥያቄዎች በተቀናጀ መንገድ ለመመለስ እንደሚሰራ ተናግረዋል።
በተለይም በተካሄደው ሀገራዊ ምክክር የተገኙ ፍሬዎች ተጠናክረው እንዲፈጸሙ የክትትልና ድጋፍ ሥራዎቻችንን ማጠናከር ይገባል ነው ያሉት።
ለዚህም የጋራ ጥረትን በማሳደግ የሕዝቡን ተጠቃሚነት ማጠናከር እንደሚገባ አመልክተዋል።