የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት 118 ነጥብ 91 ቢሊየን ብር ገቢ አገኘ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በተጠናቀቀው 2018 በጀት ዓመት ከተለያዩ የገቢ አማራጮች 118 ነጥብ 91 ቢሊየን ብር ገቢ አገኘ፡፡
የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ጌቱ ገረመው (ኢ/ር) በሰጡት መግለጫ ÷ ገቢው ከኢነርጂ ሽያጭ፣ ከአዲስ ደንበኞች መስተንግዶ፣ ከማያገለግሉ ንብረቶች ሽያጭ እና ከሌሎች ልዩ ልዩ የገቢ ምንጮች መገኘቱን ተናግረዋል፡፡
በዚህ መሰረትም ከኢነርጂ ሽያጭ 75 ነጥብ 17 ቢሊየን ብር ለማግኘት ታቅዶ የውጭ ሀገር ሽያጭን ጨምሮ 76 ነጥብ 53 ቢሊየን ብር ገቢ መገኘቱን አስረድተዋል፡፡
በተጨማሪም ከአዲስ ደንበኞች መስተንግዶ 37 ነጥብ 74 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ 39 ነጥብ 23 ቢሊየን ብር መገኘቱን ነው የገለጹት፡፡
የማያገለግሉ ንብረቶችን በመሸጥ 275 ሚሊየን ብር የተገኘ ሲሆን ÷ ከልዩ ልዩ ገቢዎች ደግሞ 2 ነጥብ 68 ቢሊየን ብር መገኘቱን አስረድተዋል፡፡
የገቢ አፈጻጸሙ 103 በመቶ መሆኑንና ከ2017 በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ88 ነጥብ 4 በመቶ እድገት ማሳየቱን አመልክተዋል፡፡
የዲጂታል ክፍያ አማራጭ የሚጠቀሙ ደንበኞች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቶ በአሁን ወቅት 95 ነጥብ 3 በመቶ መደረሱን ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ቻርጅ ማድረጊያ ጣቢያዎች ገንብቶ ወደ ስራ በማስገባትና ስራ በማስጀመር 14 ነጥብ 25 ሚሊየን ብር ገቢ ተገኝቷል ነው ያሉት፡፡
በዚህም እንደ ሀገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚን ለማሳደግና ዲጅታል ኢትዮጵያ 2030ን ለማሳካት በሚደረገው ጥረት አገልግሎቱ የላቀ ሚና እየተወጣ ነው ብለዋል፡፡
ከኢነርጂ ሽያጭ ከሚሰበሰበው አጠቃላይ ገቢ ውስጥ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ለተፈፀመው 18 ሺህ 319 ጊጋ ዋት ሰዓት የኢነርጂ ግዢ 48 ነጥብ 42 ቢሊየን ብር ክፍያ መፈጸሙን አብራርተዋል፡፡
በአጠቃላይ በበጀት ዓመቱ በመደበኛ እና በካፒታል በጀት133 ነጥብ 59 ቢሊየን ብር ስራ ላይ መዋሉን ነው ያብራሩት፡፡
ከዚህ ውስጥ 80 ነጥብ 6 በመቶ ከተቋሙ ገቢ፣ 2 በመቶ ከመንግሥት፣ 16 ነጥብ 2 በመቶ ከውጪ ድጎማ እንዲሁም 1 ነጥብ 2 በመቶ ከውጭ ብድር የተሸፈነ ነው ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል ከዋናው ግሪድና በኦፍ ግሪድ ከ205 በላይ አዲስ የገጠር ቀበሌዎችንና መንደሮችን የኤሌክትሪክ ሃይል ተደራሽ ማድረግ መቻሉን አመልክተዋል፡፡
በአጠቃላይ አዲስ ተደራሽ የሆኑትን ጨምሮ እስካሁን በገጠር ኤሌትሪፊኬሽን አቅርቦት ፕሮግራም ተጠቃሚ የሆኑ የገጠር ከተሞችና መንደሮች ቁጥር 7 ሺህ 908 ደርሷል ነው ያሉት፡፡
በመላኩ ገድፍ