Fana: At a Speed of Life!

በመደመር መንግሥት እሳቤ ተጨባጭ ውጤት ያስመዘገበው የአፋር ክልል ግብርና

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአፋር ክልል በተጠናቀቀው 2018 በጀት ዓመት ከተለያዩ ሰብሎች ከ5 ነጥብ 4 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ተሰብስቧል አሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ፡፡
የአፋር ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር፣ 5ኛ የስራ ዘመን፣ 10ኛ መደበኛ ጉባዔውን በዛሬው ዕለት ማካሄድ ጀምሯል።
አቶ አወል አርባ በዚህ ወቅት እንዳሉት ÷ በአፋር ክልል በግብርና ዘርፍ በመደመር መንግሥት እሳቤ መሰረት በተከናወኑ ሥራዎች ተጨባጭ ውጤት ተገኝቷል፡፡
በበጀት ዓመቱ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የሕዝቡን ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የተደረገው ጥረት ውጤታማ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
ከለውጡ በፊት በአፋር ክልል ለግብርና ዘርፍ ትኩረት ይሰጠው እንዳልነበር አስታውሰው ÷ በተለይም የአፈር ማዳበሪያና ሌሎች የግብርና አቅርቦቶች ለአርሶ አደሩ በበቂ ሁኔታ ተደራሽ እንደማይሆኑ አስረድተዋል፡፡
በመደመር መንግሥት ግን በክልሉ ለግብርና ዘርፍ ያለውን እምቅ አቅም በሚገባ በመለየት ምርታማነትን ለማሳደግ በቁርጠኝነት መሰራቱን አስረድተዋል፡፡
ለአብነትም በ2018 በጀት ዓመት ከ149 ሺህ 875 ሔክታር በላይ መሬት በዘር ለመሸፈን ታቅዶ 142 ሺህ 675 ሔክታር መሸፈን መቻሉን አስረድተዋል፡፡
በምርት ዘመኑ 47 ሺህ 341 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ በተገቢው ጊዜ መሰራጨቱን ጠቁመው ÷ ይህም ምርታማነትን ለማሳደግ ጉልህ ሚና ማበረከቱን አውስተዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ 5 ሚሊየን 400 ሺህ 697 ኩንታል ምርት ተሰብስቧል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ÷ አፈጻጸሙ ከተያዘው ዕቅድ 96 በመቶ መሆኑን ጠቁመዋል።
በአንጻሩ ከለውጡ በፊት በክልሉ በየዓመቱ ከ1 ሚሊየን 610 ሺህ ኩንታል የማይበልጥ ምርት ብቻ ይሰበሰብ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
በተመሳሳይ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብርን ይበልጥ በማጠናከር የክልሉን ሥነ ምሕዳር ለማደስ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በሌላ በኩል 245 ሺህ 737 ሔክታር መሬት ላይ የአፈር መሸርሸር ጥበቃና ተያያዥ ሥራዎች እንደተከናወኑ መጥቀሳቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ለፋና ዲጂታል ገልጿል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.