Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮ ኮደርስ ፤ ወጣቶች በክረምቱ ጊዜ የሚያተርፉበት ትልቅ ዕድል

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተያዘው ክረምት ወቅት የ5 ሚሊየን የኮደርስ መርሐ ግብር ወደ 7 ሚሊየን ከፍ ለማድረግ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በክረምቱ የኮዲንግ ዘመቻውን ወደ ሰባት ሚሊየን ለማድረስ ያቀረቡትን ጥሪ ተከትሎም መርሐ ግብሩ ተጠናክሮ ቀጥሏል።
በዚህም መሰረት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አስተናጋጅነት በኢኒሼቲቩ ዙሪያ የልምድ ልውውጥ መርሐ ግብር በዛሬው ዕለት ተካሂዷል።
መርሐ ግብሩ የዘርፉ መሪዎችን፣ ፖሊሲ አውጭዎችን፣ የምስክር ወረቀት ያላቸውን ተመራቂዎች እና ወጣት ባለሙያዎችን በአንድነት ያገናኘ ሲሆን÷ በሰው ሰራሽ አስተውሎት ላይ ያተኮረ የኤግዚቢሽን ጉብኝትም ተደርጎበታል።
በዝግጅቱ መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ቢልለኔ ሥዩም ÷ የወጣቶች የቴክኒክና የዲጂታል ክህሎት ብቃት ወሳኝ ሀገራዊ ሀብት መሆኑን አንስተዋል።
አያይዘውም በክረምቱ የኮደሮችን ቁጥር ሰባት ሚሊዮን ለማድረስ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀረበውን ጥሪ ተግባራዊነት አረጋግጠዋል።
መድረኩ የወጣቶችን የለውጥ ጉዞ የሚያሳዩ በርካታ አበረታች ተሞክሮዎችን የተጋሩ ሲሆን የቴክኖሎጂ ሥራ ፈጣሪዋ ማኅሌት ሥዩም ልምዳቸውን ካካፈሉ ወጣቶች መካከል አንዷ ናት።
ወጣት ማህሌት ፕሮግራሚንግን ለማወቅ የግድ የኮምፒውተር ሳይንስ ወይም ልዩ የትምህርት ዘርፍ እንደማያስፈልግና ይልቁንም ሰዎች በእጃቸው ያሉትን የኢንተርኔትና የቴክኖሎጂ መረጃዎች በመጠቀም፣ የአካባቢያቸውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በመተንተን ተግባራዊ መፍትሔ ማምጣት እንደሚችሉ አስረድታለች።
በዩኒቨርሲቲ ቆይታው የመጨረሻ ዓመታት ውስጥ ኢኒሼቲቩን የተቀላቀለው አዝመራው ታደሰ ሌላው የመርሃ ግብሩ የለውጥ ማሳያ ነው።
ኮድ ማድረግን መማር የጀመረበት ጥረት በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ ኮደሮች የሚያገናኝ ድረ-ገጽ ወደ ማበልጸግ አድጎ፤ ዛሬ ላይ ፉል ስታክ ድረ-ገጽ አልሚ መሆን ችሏል።
እንደዚሁም የቴክኖሎጂ ሥራ ፈጣሪዋ ቤተልሔም ደሴ ከ17 ዓመት በፊት ገና የአስር ዓመት ታዳጊ ሆና የዲጂታል አማራጮች ጨርሶ በማይገኙበት ሁኔታ ውስጥ የቴክኖሎጂ ሕይወቷን እንደጀመረች አስታውሳለች።
በአጠቃላይ የ 5 ሚሊየን የኢትዮ ኮደርስ መርሐ ግብር ወጣቶች በተግባራዊ ዲጂታል ክህሎት ልማት አማካኝነት ለዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 አጀንዳ ዕድገት የራሳቸውን ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ እያነሳሳ ይገኛል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) የ5 ሚሊየን ኮደርስ ኮርሶች በነጻ እንደሚገኙና የሚሰጠው የምስክር ወረቀትም ዓለም አቀፍ ዕውቅና እንዳለው መናገራቸው ይታወቃል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.