Fana: At a Speed of Life!

በአፍሪካ ሀገራት ተሞክሮ የሚወሰድበት መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ የተቀናጀ የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ ልምድ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም ከፍተኛ ተሞክሮ የሚወስዱበት ነው አሉ የኢፌዲሪ መሶብ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዮናስ አለማየሁ።

የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች የተሳለጠ አገልግሎት እየሰጠ የሚገኘውን የኢፌዴሪ መሶብ አገልግሎት ተዘዋውረው ተመልክተዋል፡፡

ዋና ስራ አስፈጻሚው ለጎብኚዎች በሰጡት ማብራሪያ÷ የኢትዮጵያ የተቀናጀ የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ ልምድ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም በቴክኖሎጂ የተደገፈ የመንግሥት አገልግሎት ሥርዓትን እንዲገነቡ ያግዛል ብለዋል።

ተበታትነው ይሰጡ የነበሩትን አገልግሎቶች ለማግኘት ዜጎች ብዙ ተቋማት ጋር እንዲሄዱ እና ጊዜ እና ግንዘባቸውን እንዲያባክኑ ያደርግ እንደነበር አንስታዋል፡፡

ይህን ችግር ለመፍታት መሶብ የተለያዩ የመንግሥት ተቋማትንና አገልግሎቶችን በአንድ ማዕከል በማቀናጀት የአንድ መስኮት አገልግሎት አሰጣጥን በተግባር እያስፋፋ መሆኑን አብራርተዋል።

የመሶብ አገልግሎት ከአንድ ማዕከል አገልግሎት በመነሳት ወደ ተንቀሳቃሽና የቤት ለቤት አገልግሎት እንዲሁም ወደ ዲጂታል መድረክ መስፋፋቱን አስረድተዋል።

በተለይም “ዩኒፋይድ መሶብ” የተሰኘው የኦንላይን መድረክ ዜጎች በሞባይል ስልካቸው የመንግሥት አገልግሎቶችን በቀላሉ እንዲያገኙ የሚያስችል ሥርዓት መሆኑን አመልክተዋል፡፡

መሶብ የአንድ ማዕከል የዲጂታል አገልግሎትን ተሞክሮ ከኢትዮጵያ ውጭ ለማስፋፋት እየተሰራ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡

በቀጣይ ከጅቡቲ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ኬንያና ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ጋር በዲጂታል የመንግሥት አገልግሎት ዙሪያ ትስስር በመፍጠር የአህጉራዊ ዲጂታል ሥርዓት መገንባት የመሶብ ራዕይ እንደሆነም አስገንዝበዋል፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.