Fana: At a Speed of Life!

አማራውን ትምክህተኛ፣ ኦሮሞውን ጠባብ ብሔርተኛ፤ ሌሎችን በአጋርነት ያገለለው የሕገ ወጡ ቡድን የፖለቲካ ቁማር የቅርብ ጊዜ ትውስታ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ዘመናዊ የፖለቲካ ታሪክ በርካታ ውጣ ውረዶችንና የሥርዓት ለውጦችን ያስተናገደ ነው።

ከእነዚህም መካከል የሕገ ወጡ የህወሓት መራሹ የኢሕአዴግ የሥልጣን ዘመን በሀገሪቱ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መዋቅር ላይ ጥልቅ ጠባሳ ጥሎ ማለፉ ይታወሳል።

ሥርዓቱ ሥልጣን ላይ በነበረበት ወቅት ይከተለው የነበረው የከፋፍለህ ግዛ መርህ፣ የማሸማቀቅና የማግለል ፖለቲካ፣ በሕዝቦች መካከል አብሮነትን ከማጠናከር ይልቅ መጠራጠርንና ቂምን እንዲዘሩ አድርጓል።

በወቅቱ ሕገ ወጡ ሕወሓት የፖለቲካ የበላይነቱን ለማስጠበቅ ሲል የተጠቀመበት ዋነኛው መሣሪያው ብሔርን መሠረት ያደረገ የማሸማቀቂያ ታርጋ መለጠፍ ነበር።

አማራውን ስልታዊ በሆነ መንገድ “ትምክህተኛ” እያለ በመፈረጅ፣ በታሪክ ውስጥ ላልተፈጸሙ ስህተቶች ሁሉ ተጠያቂና ባለዕዳ አድርጎ የማቅረብ ሥራ ሠርቷል።

ይህ ፍረጃ ማኅበረሰቡ በሀገሪቱ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ ባለው ዕምነት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሯል።

በተመሳሳይ መልኩ የኦሮሞን ሕዝብ መሠረታዊ የመብትና የማንነት ጥያቄዎችን ለማፈን “ጠባብ” የሚል ስም በመስጠት ያሸማቅቅ ነበር።

ይህም ሕዝቡ መብቱን እንዳይጠይቅና በነፃነት እንዳይንቀሳቀስ ለማድረግ የታለመ ስልታዊ ሥነ ልቦናዊ ጫና ለማሳደር ያለመ ነው።

በወቅቱ በነበረው የሕግ የበላይነት መታወክ የሰብዓዊ መብት ረገጣ በግልጽ በሀገሪቱ ማረሚያ ቤቶች ውስጥ ይታይ ነበር።

በወቅቱ የነበሩትን የፖለቲካ እስረኞች ቁጥር ብዛትና ስብጥር ስንመለከት፣ ትልቁን ድርሻ የሚይዙት የኦሮሞና የአማራ ተወላጆች ነበሩ።

በተለይም በፌዴራል ማዕከላዊ እስር ቤቶች ውስጥ የሚታሰሩ ዜጎች ቁጥር ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ “የእስር ቤቶች ቋንቋ አፋን ኦሮሞ ነው” እስኪባል ድረስ የጅምላ እስርና እንግልት ይፈጸም ነበር።

አማራውና ኦሮሞው በኢሕአዴግ ግንባር አባልነት ስም በብአዴንና ኦሕዴድ አማካኝነት ቢታቀፉም፣ ውሳኔ ሰጪነታቸውና ከሀገሪቱ ኢኮኖሚ የሚያገኙት ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ግን እጅግ የተገደበ ነበር። መዋቅሩ የፊት መሸፈኛ እንጂ እውነተኛ ውክልና አልነበረውም።

የሥርዓቱ አግላይነት በሁለቱ ትላልቅ ብሔሮች ላይ ብቻ የተወሰነ አልነበረም። ይልቁንም በሀገራቸው ሁለተኛ ዜግነት የተሰጣቸው በርካቶች ነበሩ፡፡

የትግራይ ተወላጆችም ቢሆኑ በሕገ ወጡ ቡድን ስብስብ ተነገደባቸው እንጂ አንዳች የተጠቀሙት ነገር አልነበረም፡፡ ከአራቱ መስራች ድርጅቶች (ከትግራዩ ሕወሓት፣ ከአማራው ብአዴን፣ ከኦሮሚያው ኦህዴድና ከወቅቱ የደቡብ ክልል ደኢህዴን) ውጪ የነበሩት እንደ አፋር፣ ሶማሌ፣ ጋምቤላ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና ሐረሪ ያሉ ክልሎች “አጋር” በሚል ስያሜ ከዋናው የውሳኔ ሰጪነት ሚና ተገልለው ነበር።

እነዚህ ማኅበረሰቦች በሀገሪቱ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ላይ የመወሰን መብት ተነፍገው፣ የራሳቸውን ክልል እንኳ በነፃነት ማስተዳደር የማይችሉበትና የሁለተኛ ዜጋ ያህል የሚቆጠሩበት ሥርዓት ሰፍኖ ነበር።

ይህ የታሪክ በደል አግባብ አለመሆኑን በመረዳት፣ መላው የሀገሪቱ ሕዝብ እና ከኢሕአዴግ አባላት ውስጥ እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አይነት ቆራጥ መሪዎች ሕይወታቸውን አስይዘው ሀገራዊ ለውጡ እውን እንዲሆን አድርገዋል፡፡

ግብዓተ መሬቱ የተቃረበው ሕገ ወጡ ሕወሓት፣ ዛሬ እንደ ትናንት እየመሰለው አይኑን በጨው ታጥቦ ያለፈ የጎደፈ ታሪኩ የተረሳለት እየመሰለው፣ እርጅናውን እየታገለ ከእሱ አይነት ባንዳዎች እና ከባእዳን ታሪካዊ ጠላቶች ጋር በማበር ከዘራ ተደግፎ ቆመህ ጠብቀኝ ለመጎተት ይሞክራል፡፡

ሕገ ወጡ ህወሓት በፌዴራል መንግሥት ሥልጣን ላይ እያለ የብሔር ልዩነትን እንደ ሀገራዊ ውበት ሳይሆን፣ ለግል ቡድኑ የፖለቲካ ሥልጣን ማራዘሚያነት ለመከፋፈልና ለማዳከም ይጠቀምበት ነበር።

አማራውን በትምክህተኝነት፣ ኦሮሞውን በጠባብ ብሔርተኝነት ፈርጆ ማሸማቀቅ፣ እስር ቤቶችን በአንድ ብሔር ተናጋሪዎች መሙላትና ሌሎችን አጋር በማድረግ ማግለል የሥርዓቱ መገለጫዎች ነበሩ።

ይህ አካሄድ ሕዝቦች በሀገራቸው ፍትሐዊ ተጠቃሚ እንዳይሆኑና እርስ በርሳቸው እየተጠራጠሩ እንዲቆዩ አድርጓቸዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.