ቴክኖሎጂን ከጀግንነት ያጣመረው የኢትዮጵያ የሉዓላዊነት ምሽግ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 18፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሀገሪቱን ጥንታዊ የታሪክ አደራ፣ ሉዓላዊነት እና የሕዝቦቿን የማይበገር ጽናት ዐሻራ የያዘ የሀገራዊ ታላቅነት ሕያው ተምሳሌት ነው።
ከዓድዋ ድል ጀምሮ እስከ ዛሬው ዘመናዊ ወታደራዊ አደረጃጀት ድረስ ሠራዊቱ የሀገርን ድንበርና የሕዝብን ደኅንነት ከመጠበቅ ባለፈ የኢትዮጵያውያንን ኅብረ ብሔራዊ ጥንካሬና ነፃነት የሚያንጸባርቅ ትልቅ ሀገራዊ ተቋም ሆኖ ቀጥሏል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የአባቶችን የመከታነት እና የጀግንነት ታሪክ ተረካቢ ብቻ ሳይሆን የሀገሪቱን ታላቅነት በጽናት የሚያስቀጥል የማንነት እና የነፃነት መሠረት ነው።
በአሁኑ ወቅት ሠራዊቱ በሰው ኃይል ብቃት ብቻ ሳይሆን በወታደራዊ ቴክኖሎጂ እና በሀገር በቀል ኢንዱስትሪዎች ዕድገት ረገድ ትልቅ ሽግግር እያደረገ ይገኛል።
እንደ ሆሚቾ ተተኳሽ ማምረቻ እና ስካይዋርድ ኤሮኖቲክስ ባሉ ሀገር በቀል ተቋማት አማካኝነት የሰው አልባ አውሮፕላኖችን በሀገር ውስጥ የማምረት፣ የከባድ መሣሪያዎችንና ታንኮችን በሪቨርስ ምሕንድስና የማደስ እና የማሻሻል አቅምን አጎልብቷል።
ከዚህም ባሻገር ከሰው ሰራሽ አስተውሎት እና ከሳይበር ደኅንነት ጋር የተደረጉ ዘመናዊ ትስስሮች ሠራዊቱ የዘመኑን ወታደራዊ ሥጋቶች በራሱ አቅም እና ዕውቀት በብቃት ለመመከት የሚያስችለውን ስትራቴጂያዊ ራስን መቻል አጎናጽፈውታል።
ይህ ኅብረ-ብሔራዊ ሠራዊት ከብሔር፣ ከፖለቲካ እና ከሀይማኖት ውግንና ገለልተኛ በሆነ መንገድ የተዋቀረና የኢትዮጵያውያን ሁሉ መመኪያ የሆነ የሀገራዊ አንድነት መገለጫ ነው።
ከሁሉም የሀገሪቱ ማዕዘናት የተውጣጡ በወታደራዊ ሳይንስ እና በሥነ ምግባር የሠለጠኑ ጀግኖች የተሰለፉበት ተቋም በመሆኑ የሀገሪቱ የመጨረሻው የሉዓላዊነት ምሽግ ሆኖ ያገለግላል።
በተለይም የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ፣ የአየር ወለድ እና የባህር ኃይል አደረጃጀቶች ግንባታ የሠራዊቱን ፈጣን ተንቀሳቃሽነት እና የማጥቃት አቅም በከፍተኛ ደረጃ አሳድገውታል።
ሀገርን ከመጠበቅ አልፎ በአፍሪካ ኅብረት የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ተሰማርቶ ለቀጣናዊ ሰላም መሥዋዕትነት በመክፈል የኢትዮጵያን አህጉራዊ ተጽዕኖ ፈጣሪነት እና የሰላም አምባሳደርነት አጽንቶ ቀጥሏል።
በአጠቃላይ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በታሪክ የተፈተነ፣ በዘመናዊ ሳይንስና ቴክኖሎጂ የጎለበተ እንዲሁም በራስ አቅም የመቆም አርማን የተጎናጸፈ ተቋም ነው።
ሠራዊቱ ቴክኖሎጂን ከጀግንነት፣ ሙያዊ ብቃትን ከሀገር ፍቅር ጋር አጣጥሞ በመያዝ የኢትዮጵያን ሰላም፣ ልማት እና ዘላቂ ታላቅነት የሚያረጋግጥ ተቋም በመሆን በኢትዮጵያ ላይ የሚቃጡ ማናቸውንም ዓይነት ስጋቶች የሚመክት ሕያው ጋሻ ሆኖ በኩራት ቆሟል።
በአብረሃም አበራ