በእሳት የተፈተነው፣ የኢትዮጵያ የሉዓላዊነት ደጀን
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአንድ ሀገር ሕልውና፣ የሕዝቦች ነጻነትና ዘላቂ ልማት መሰረቱ ዘላቂ ሰላምና አስተማማኝ ደህንነት መኖር ነው።
በረጅም የሀገረ መንግሥት ታሪኳ በርካታ ታላላቅ ውጣ ውረዶችን፣ የውጭ ወረራዎችንና የውስጥ ፈተናዎችን ያሳለፈችው ኢትዮጵያ፣ የሉዓላዊነቷና የዳር ድንበሯ አስተማማኝ ዘብ ሆኖ የዘለቀው ዋነኛው የደህንነት አምዷ የኢትዮጵያ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ነው።
መከላከያ ሰራዊቱ የሀገርን ድንበር ከመጠበቅ አልፎ የሕዝቦችን አንድነት፣ ሰላምና ብሄራዊ ክብር የሚያስጠብቅ፣ ታሪካዊና ሕዝባዊ እሴቶችን አዘምኖ ያስቀጠለ የጽናት ማህተም ነው።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ታሪካዊ መሰረቱ ከጥንታዊቷ ኢትዮጵያ የነጻነት ተጋድሎ ጋር የተያያዘ ነው።
በተለይም በታሪካዊው የዓድዋና ተጋድሎና በሌሎች ታላላቅ ሀገራዊ የታሪክ ምዕራፎች የተሰነዱ የሕዝብ አጋርነትና ፍጹም ሀገር ወዳድነት የታየባቸው ኩነቶች ውስጥ ሠራዊቱ ድርሻው የጎላ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የወል ማንነትና ሕብረ ብሔራዊ አንድነት መገለጫ የሆነው ይህ ሠራዊት፣ የሀገርን ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓትና የግዛት አንድነት የማስከበር ከፍተኛ ሃላፊነት በመወጣት ታሪክ በመጻፍ ጉዞው ቀጥሏል።
የሠራዊቱ አባላት ከሁሉም የሀገሪቱ ማዕዘናት የተወጣጡ በመሆናቸውና የሠራዊቱ ጥንካሬ የሚያንጸባርቀው የመላው ኢትዮጵያውያንን ጥንካሬና ህብረትን መሆኑ ግልጽ ነው።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ጥንካሬና ዝና በሀገር ውስጥ ወታደራዊ ግዳጆች ብቻ የተወሰነ አይደለም።
በተለያዩ የአፍሪካና የዓለም ክፍሎች በተካሄዱ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና የአፍሪካ ህብረት የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ላይ ያሳየው የላቀ የሙያ ብቃት፣ ሥነ ምግባርና ሰብዓዊነት ሀገራችን በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ምስጋናና ክብር እንዲቸራት አድርጓል።
ለአብነት ያክልም በኮሪያና በኮንጎ በ20ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ የታየው ፍጹም ወታደራዊ ጀግንነት፣ በሩዋንዳና በቡሩንዲ በከባድ ሰብዓዊ ጥፋቶች ወቅት ያሳየው የዜጎችን ሕይወት የመታደግ ስራ፣ በደቡብ ሱዳን እና በሶማሊያ የቀጣናውን ሰላም ለማስከበርና ሽብርተኝነትን ለመታገል የተከፈለ ታላቅ መስዋዕትነት በዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ዘንድ ኢትዮጵያን ባለ ውለታ ያደረጉ ዘመቻዎች ነበሩ፡፡
የኢትዮጵያ ሀገር መከላከያ ሠራዊት የሀገር ሕልውና፣ የነጻነትና የታሪክ እሴቶች ጠባቂ ነው። በከፍተኛ ሥነ ምግባር፣ በሙያዊ ብቃትና በሀገር ፍቅር የታነጸው ይህ ሰራዊት፣ የሀገሪቱን ሰላም፣ ደህንነትና ሉዓላዊነት በጽናት በመጠበቅ ረገድ የማይናወጥ አቋም አለው።
በዘመናችን ወታደራዊ ስጋቶች መልካቸውንና ባሕሪያቸውን እየቀየሩ በመጡበት ሁኔታ፣ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊትም ራሱን በዘመናዊ የጦር ሳይንስ፤ በላቀ ቴክኖሎጂና የመረጃ ሥርአቶች አደራጅቶ ይገኛል።
በመሬትም ሆነ በአየር የውጊያ አቅምን በማሳደግ፣ የሰው ሃይልን ጥራት ባለው ስልጠና ብቁ በማድረግ እንዲሁም የጦር መሳሪያዎችን በሀገር ውስጥ የማምረትና የመጠገን አቅምን በማጎልበት፤ ኢትዮጵያ ከማንኛውም አይነት ስጋት ራሷን በብቃት እንድትከላከል የሚያስችል አቅምን ገንብቷል።
በመሆኑም ግርማ ሞገሱ ጠላትን የሚያስፈራው ሠራዊቱ የሀገር ሰላምና ሕልውና አስተማማኝ ዋስትና፣ የሕዝቦች ህብረት መገለጫ እና የእውነትም የኢትዮጵያ የሉዓላዊነት ደጀን በመሆን በጽናት ቆሟል፡፡
በመልካም ፈቃዱ