አዲስ አበባ፤ በዲፕሎማሲ የደመቀችው ከተማ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የፖለቲካ እና የዲፕሎማሲው ዘርፍ ዓለም አቀፋዊ ገጽታዋ የሆኑት አዲስ አበባ ከተማ ዘርፈ ብዙ በርካታ መድረኮችን እያስተናገደች ትገኛለች።
በየዓመቱ የዓለም መሪዎች፣ ታዋቂ ዲፕሎማቶች፣ ተመራማሪዎች እና የተለያየ ዘርፍ ባለሙያዎች የሚጎርፉባት አዲስ አበባ ታላላቅ ዓለም አቀፍ መድረኮች በስኬት በማስተናገድ የዲፕሎማሲ አቅሟን፣ አስተማማኝ ሰላሟን እና የኮንፈረንስ ቱሪዝም ዕድገቷን ለዓለም ማሳየት ችላለች።
ከተማዋ የአፍሪካ ህብረት እና የተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ቋሚ መቀመጫ በመሆኗ፣ የአፍሪካን የወደፊት ዕጣ ፈንታ የሚወስኑ ታሪካዊ ውሳኔዎች የሚስተናገዱባት ስፍራ ሆናለች።
በየዓመቱ የሚካሄደው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ እና በተመድ ዋና ጸሐፊና በአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር መሪነት የሚካሄደው የተባበሩት መንግሥታት እና የአፍሪካ ህብረት ዓመታዊ የጋራ ጉባኤ ከተማዋ ያላትን ከፍተኛ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ የዲፕሎማሲ ተሰሚነት በተግባር ያረጋገጡ መድረኮች ናቸው።
ከተማዋ በታሪኳ ካስተናገደቻቸው ታላላቅ መድረኮች መካከል በቅርቡ በየካቲት 2018 ዓ.ም የተካሄደው የሁለተኛው የጣሊያን-አፍሪካ ጉባኤ በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል።
በጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ እና በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በጋራ የተመራውና የአውሮፓና አፍሪካን ግንኙነት ያጠናከረው ይህ ስብሰባ፣ የጣሊያንን የማቲ ፕላን ውጤታማነት ለመገምገም ለመጀመሪያ ጊዜ ከአውሮፓ ውጭ በአፍሪካ የተካሄደ ታሪካዊ ጉባኤ ነው።
ይህም አዲስ አበባ በአህጉሪቱና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን የስትራቴጂክ ድልድይነት ሚና ይበልጥ ያጎላ ክስተት ሆኖ ተመዝግቧል።
ከፖለቲካው ባሻገር አዲስ አበባ ለዓለም አቀፍ የንግድ፣ የልማት፣ የጤና እና የማኅበራዊ ውይይቶች ዋነኛ መዳረሻ ሆና እያገለገለች ትገኛለች።
በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አስተባባሪነት የተካሄደው የዓለም አቀፍ የፍልሰት ስምምነት አህጉራዊ ስብሰባ በስኬት አስተናግዳለች።
ከ46 በላይ የአፍሪካ ሃገራት የተውጣጡ ከ750 በላይ ባለድርሻ አካላትና የሕክምና ተቋማት ተወካዮች የተሳተፉበትን ሁለተኛው የአፍሪካ የሕክምና ትምህርት አህጉራዊ ጉባኤ በስኬት ማስተናገድ ችላለች።
እነዚህን እጅግ በጣም በርካታ ቁጥር ያላቸውን ተሳታፊዎች የሚይዙ ታላላቅ መድረኮችን በስኬት ለመምራት የአዲስ አበባ ዘመናዊ የጉባኤ መሰረተ ልማቶች ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።
በሶስና አለማየሁ