እርስ በርሳቸው የማይተማመኑ የጥፋት ሃይሎች ከንቱ ጥምረት – “ጽምዶ”
ሕገ ወጡ የህወሓት ቡድን ከሻዕቢያና ሌሎች ጽንፈኛ ሃይሎች ጋር “ጽምዶ” የተሰኘ በፖለቲካዊ ተቃርኖ የተሞላ የጥፋት ጥምረት በመመስረት የትግራይ ሕዝብን ለሁለንተናዊ ቀውስ ለመዳረግ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡
”ጽምዶ” በሚል ጥምረት በመፍጠር የኢትዮጵያን ሰላም ለማደፍረስ የሚንቀሳቀሰው የጥላቻ ኃይል በጋራ ፖለቲካዊ ራዕይና በሕዝብ ጥቅም ላይ የተመሠረተ አይደለም፡፡
የሕዝብ ጠላትና የጥፋት ጥምረት የሆነው ጽምዶ የመንግሥትን አቅም ለማዳከም በጊዜያዊ የሥልጣን ስሌት የተፈጠረ ዘመኑን ያልዋጀ የአሮጌ አስተሳሰብ ተሸካሚዎች ስብስብ ነው፡፡
ይሁን እንጂ በፖለቲካዊ ቅራኔና በርዕዮት ዓለም ልዩነት የተከፋፈሉ እነዚህ ኃይሎች በጊዜያዊ የጋራ ጥቅም ዙሪያ የፈጠሩት ጥምረት የኢትዮጵያን የሰላምና የጥንካሬ ጉዞ ከቶ ሊያስቆም አይችልም።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቅርቡ እንዳሉት ÷ጥምረቱ የተፈጠረው የመንግሥት የሕግ የበላይነት የማስከበር አቅም እየጠነከረ በመምጣቱ የጥፋት ሃይሎቹ በደረሰባቸው የመክሰም ስጋት የተነሳ ነው፡፡
ኢትዮጵያ የጀመረችውን የብልጽግና እና የሰላም ጉዞ ለማስተጓጎል የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ጥምረት ጽምዶ በምንም መልኩ በጋራ እሴት ወይም በፖለቲካዊ ራዕይ ላይ የተመሰረተ አይደለም።
በእነዚህ ኃይሎች መካከል ያለው ታሪካዊ መሠረትም ጥላቻ እንጂ ትብብር እንዳልሆነ የአደባባይ እውነት ነው፡፡
በተመሳሳይ ከዚህ በፊት እርስ በርሳቸው የማይተማመኑ በጫካ ያሉ ታጣቂዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ የጋራ መርህ እና ግብ ማሳካት የማይችሉ እና ፈጽሞ የማይታሰብ የፖለቲካ ቅዠት መመስረታቸውን በተደጋጋሚ ይፋ ሲያደርጉ ይስተዋላል።
ይህ የቆሞ ቀሮች ስብስብ ትናንት እርስ በርስ ሲካሰሱ የነበሩ ሃይሎች ለእኩይ አላማ የፈጠሩት ጥምረት ነው፡፡
የከሰረው ሕገ ወጡ ህወሓት ነፍጥ አንግበው ጫካ ከገቡ ቡድኖች ጋር በመሆን ቆምንለት ከሚሉት የሕዝብ ፍላጎት በተቃረነ መልኩ የነበራቸውን አላማ በመርሳት የጥፋት ትብብር ለመፍጠር መሞከራቸውም ሕዝብን ከመናቅ የሚመነጭ ነው፡፡
የጥፋት ቡድኖቹ ሃይላቸው በሀገር ውስጥ እየተመናመነና እየተዳከመ ሲመጣ ሚዛናዊ ወዳልሆነ ጽንፍ መሄዳቸው የማይቀር ነው።
ሕገ ወጡ ህወሓት እና ኤርትራ ለበርካታ አሥርት ዓመታት በከረረ የጠላትነት ዑደት ውስጥ የኖሩ ኃይሎች መሆናቸው ይታወቃል፡፡
እንዲሁም እንደ ግብፅ ያሉ ታሪካዊ የውጭ ጠላቶች ጋር በአንድ ጥላ ስር መሰባሰባቸው የቡድኖቹን መርሕ አልባነት እና የፖለቲካ ግብዝነት ቁልጭ አድርጎ ያሳያል።
ራሱን ”ጽምዶ” ሲል የሰየመው እኩይ ኃይል ለዘመናት የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላት የሆነችውን ግብጽ ፍላጎት እንኳን ቆም ብሎ ማዬት አልፈለገም።
የግብጽ አንዱና ብቸኛ ስልታዊ ፍላጎት የዓባይ ወንዝ ውሃ አጠቃቀምን እና የሕዳሴ ግድብን መቆጣጠር ሲሆን÷ የሀገር ውስጥ ኃይሎች ዓላማ ደግሞ ሌላ ነው።
ቡድኖቹ ፈጽሞ የማይገናኙ እና አንዱ የሌላውን ሕልውና የሚጻረሩ በመሆናቸው የመሰረቱት ጥምረትም ከንቱና ከሕዝብ ጥቅም በተቃራኒ የቆመ ነው፡፡
የመርሕ አልባዎቹ ጊዜያዊ ኅብረት የኢትዮጵያን የጥንካሬ ጉዞ ሊያስቆም የማይችል ነው፤ መሬት ላይ ያለው እውነታም የመንግሥት የሕግ የበላይነት የማስከበር አቅም እየጠነከረ መምጣቱን ያስረግጣል።
የጥፋት ሃይሎች ጽምዶ በሚል የሚጠሩት ያልተቀደሰ ጋብቻ በወረቀት ላይ ወይም በፕሮፓጋንዳ ደረጃ ሊፈጠር ቢሞክርም አባላቱ በታሪክ ባላቸው ጥላቻ፣ በፖለቲካዊ ድክመትና በርዕዮተ ዓለም ቅራኔ ረጅም ርቀት መጓዝ አይችሉም፡፡
ጥምረቱ የመንግሥትን የተጠናከረ ሕግ የማስከበር ክንድ መቋቋም ያቃታቸው የጥፋት ሃይሎች ላለመክሰም ብሎም የሕዝብን ድጋፍ ለማግኘት የሞከሩት ከንቱ ቅዠት እንጂ ለቀጣናው ሕዝብ ጥቅም የቆመ አለመሆኑም እሙን ነው፡፡
በምንይችል አዘዘው