ክልሎች የሰብዓዊ ድጋፍ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ የሚያስችል ስራ እየሰሩ ነው
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ክልሎች የሰብዓዊ ድጋፍ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ የሚያስችል ስራ እየሰሩ ነው አለ የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን፡፡
ኮሚሽነር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ/ር) እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ የሰብዓዊ ድጋፍ ሉዓላዊነትን የማረጋገጥ እመርታ የተረጂነት አስተሳሰብን በመስበር ወደ አዲስ የምርታማነት ምዕራፍ እያሸጋገረ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ክልሎች የሰብዓዊ ድጋፍ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ የሚያስችል ስራ እየሰሩ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በኢትዮጵያ የሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎችን ቀድሞ በመከላከልና አደጋ ሲደርስ ፈጣን ምላሽ በመስጠት ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም መሸፈን የሚያስችል የአሰራርና የሕግ ማሻሻያ መደረጉን ገልጸዋል፡፡
ይህም ዜጎችን ከተረጂነት አመለካከት በማላቀቅ የአደጋ ተጋላጭነትንና የሰብዓዊ ድጋፍ ተጠቃሚዎችን ቁጥር በመሠረታዊነት መቀነስ በማስቻል እመርታዊ ውጤት እያስገኘ ነው ብለዋል።
በዓለም አቀፍ አጋር አካላት ላይ የተመረኮዘውንና ዋስትና የማይሰጠውን የሰብዓዊ ድጋፍ ምላሽ በራስ አቅም በመሸፈን የሰብዓዊ ድጋፍ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ትልቅ የታሪክ ለውጥ መፈጠሩንም ጠቁመዋል።
ባለፉት የለውጥ ዓመታት የአደጋ ስጋት አመራር ፖሊሲ በማውጣት፣ አዋጆችንና መመሪያዎችን በመከለስ ዜጎችን ከተረጂነት ለማላቀቅ በትኩረት መሰራቱንም አብራርተዋል።
ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም መሸፈን የኢትዮጵያንና የሕዝቦቿን ክብር ከማስጠበቅ ባሻገር ነፃነትንና የተሟላ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ወሳኝ መሰረት እየጣለ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለመሸፈን በተደረገው ጥረትም የሰብዓዊ ድጋፍ ፈላጊዎችን ቁጥር በ2013 ዓ.ም ከነበረበት 27 ሚሊየን በ2018 ዓ.ም ወደ 2 ነጥብ 4 ሚሊየን ዝቅ ማድረግ መቻሉን አስረድተዋል፡፡