Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ የሕፃናት ትምህርት፣ ብቁ፣ ንቁና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ትውልድ ለመፍጠር እየተሠራ ነው

 

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአንድ ሀገር ዘላቂ ልማት፣ ሰላምና ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነት የሚወሰነው ዛሬ ላይ ለሚገነባው ትውልድ በሚጣለው መሠረት ላይ ነው።

ሕፃናት የአዕምሯቸው ዕድገት ፈጣንና የሚሰጣቸውን ዕውቀት በቀላሉ የሚቀስሙበት የዕድሜ ክልል ላይ ያሉ በመሆኑ፣ በዚህ ወቅት የሚደረግ እቅድና ኢንቨስትመንት ብቁ ዜጋን ለመፍጠር ወሳኝ ሚና አለው።

ኢትዮጵያም ይህንን እውነታ በመረዳት፣ ባለፉት ስምንት ዓመታት ተወዳዳሪና ብቁ ትውልድ ለመቅረጽ በሕፃናት ትምህርት ላይ ትኩረት አድርጋ ሰፊና ተስፋ ሰጪ ሥራዎችን ስታከናውን ቆይታለች።

ሕፃናት ወደ መደበኛ አንደኛ ክፍል ከመግባታቸው በፊት በቅድመ መደበኛ ትምህርት የአዕምሮና የማኅበራዊ ዝግጁነት እንዲኖራቸው የማድረጉ ሥራ ባለፉት ስምንት ዓመታት ትልቅ ስኬት የታየበት ዘርፍ ነው።

ቀደም ሲል የቅድመ መደበኛ ትምህርት በግል ተቋማትና በከተሞች ብቻ የተወሰነ የነበረ ቢሆንም፣ በመንግሥት ጥረት መርሐ ግብሩ ወደ ገጠርና ወደ ሁሉም የመንግሥት ትምህርት ቤቶች እንዲስፋፋ ተደርጓል።

ለዚህም እንደ ምሳሌ መጥቀስ የሚቻለው በዋና ከተማዋ አዲስ አበባና በተለያዩ ክልሎች ደረጃቸውን የጠበቁ ዘመናዊ የሕፃናት ማሳደጊያና ማስተማሪያ ማዕከላት በስፋት መገንባታቸው ነው።

እነዚህ ማዕከላት ሕፃናት በተደራጀና ጨዋታን መሠረት ባደረገ መልኩ የዕውቀት መጀመሪያቸውን እንዲቀስሙ በማድረግ ረገድ ተጨባጭ ለውጥ አምጥተዋል።

በትምህርት ገበታ ላይ ውጤታማና ተወዳዳሪ ትውልድ ለመፍጠር የሕፃናት አካላዊና አዕምሯዊ ጤንነት ቀዳሚው ጉዳይ ነው።

ባለፉት ስምንት ዓመታት በሕፃናት ትምህርት ላይ ከተመዘገቡት አርአያነት ያላቸው ትልልቅ ስኬቶች መካከል የአንደኛ ደረጃና የቅድመ-መደበኛ ሕፃናት የምገባ ፕሮግራም አንዱ ነው። ይህም በአዲስ አበባና በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች እየተተገበረ ይገኛል፡፡

የተማሪዎች የምገባ ፕሮግራም በምግብ እጥረት ምክንያት ትምህርታቸውን የሚያቋርጡ ሕፃናት ቁጥርን በከፍተኛ ደረጃ የቀነሰ ከመሆኑም በላይ፣ ሕፃናት በትምህርታቸው ላይ ሙሉ ትኩረት እንዲያደርጉና ብቁ ሆነው እንዲያድጉ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መሠረት ጥሏል።

ከኢኮኖሚና ከተደራሽነት ባሻገር፣ የትምህርትን ጥራት ማሻሻልና ከዘመኑ ጋር ማገናኘት የባለፉት ስምንት ዓመታት ሌላው ትኩረት ነበር። የሕፃናትን አዕምሯዊ ብስለትና የፈጠራ ክህሎት የሚያነቃቁ አዳዲስ ሥርዓተ-ትምህርቶች ተቀርጸው ሥራ ላይ ውለዋል።

ሕፃናት በራሳቸው ቋንቋና አካባቢያዊ እውነታዎችን ባገናዘበ መልኩ እንዲማሩ የተደረገው ጥረት ለዚህ ማሳያ ነው።

በተጨማሪም፣ የመማሪያ መጻሕፍት አቅርቦትና የመምህራን አቅም ግንባታ ሥልጠናዎች በስፋት መከናወናቸው፣ ሕፃናት ከጅምሩ ተወዳዳሪ የዕውቀት አቅም ይዘው እንዲያድጉ ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል።

ባለፉት ስምንት ዓመታት የመደመር መንግሥት በኢትዮጵያ የሕፃናት ትምህርት ላይ ያከናወናቸው ተግባራት ብቁ፣ ንቁና በዓለም አቀፍ መድረክ ተወዳዳሪ ሊሆኑ የሚችሉ ዜጎችን ለመፍጠር የተጣሉ ጠንካራ መሠረቶች ናቸው፡፡

የቅድመ-መደበኛ ትምህርት ተደራሽነት፣ የተማሪዎች ምገባ ፕሮግራም እና የሥርዓተት ምህርት ማሻሻያዎች ዘርፉን ከነበረበት ዝቅተኛ ደረጃ ወደ ተሻለ ምዕራፍ አሸጋግረውታል።

ይህ የተጀመረው በጎ ተሞክሮ ተጠናክሮ መቀጠሉና በጥራት ላይ ይበልጥ መሥራት፣ የሀገሪቱን የነገ ተስፋ በፅኑ መሠረት ላይ ለመገንባትና ዘላቂ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ወሳኝ ርምጃ ነው።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.