Fana: At a Speed of Life!

የሁለተኛ ትውልድ ዳያስፖራ ልዑክ የኢትዮጵያ ጉዞውን ጀምረ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያንንና ቤተሰቦቻቸውን ያካተተ ልዑክ ዛሬ ከካናዳ ወደ ኢትዮጵያ ጉዞውን ጀምሯል።
በካናዳ የኢትዮጵያ አምባሳደር ቴዎድሮስ ግርማ ልዑኩ ከቶሮንቶ ፒርሰን ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲነሳም አሸኛኘት አድርገዋል።
በዚሁ ወቅት አምባሳደሩ ይህ ዓይነቱ ጅማሮ የዳያስፖራውን ትውልድ ከኢትዮጵያ ታሪክ፣ ባህልና ማንነት ጋር በማቀራረብ የሚኖረውን ፋይዳ ተናግረዋል።
ልዑኩ በኢትዮጵያ የአንድ ወር ቆይታ የሚያደርግ ሲሆን፣ በቆይታውም ከባህል ልውውጥና ከሃገራዊ ትውውቅ ባሻገር በክረምት በጎ ተግባራት ላይ በመሳተፍ ለማህበረሰቡ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጅት የሚያደርግ ይሆናል ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በውጭ ሃገር ያል ኢትዮጵያዊ ሃገራቸውን እንዲያዩ ሲሉ በተደጋጋሚ ጥሪ ማድረጋቸውን አስታውሰዋል።
ዛሬ ሽኝት የተደረገለት የሁለተኛ ትውልድ ዳያስፖራ ልዑክ ጉዞም ከሃገራቸው ታሪክ፣ ባህልና ማንነት ጋር ያላቸውን ትስስር እንዲያጠናክሩ የሚረዳ ነው ሲሉ አስረድተዋል።
አምባሳደር ቴዎድሮስ ይህ ጉዞ በኢትዮጵያና በዳያስፖራው መካከል የጋራ መግባባት፣ ወዳጅነትና ትብብርን የሚያጎለብቱ የህዝብ-ለህዝብ ዲፕሎማሲ ድልድዮችን ለመገንባት የሚያግዝ ነው ሲሉ አመልክተዋል።
የልዑኩ አስተባባሪ አሸናፊ ግርማና የልዑኩ አባላት በበኩላቸው፣ ይህ ጉዞ ለተሳታፊዎቹ የኢትዮጵያን ባህልና ታሪክ በቀጥታ ለመለማመድ፣ ከሀገራቸው ጋር ያላቸውን ትስስር ለማጠናከርና በበጎ ተግባራት በመሳተፍ ለማህበረሰቡ አስተዋጽኦ ለማድረግ ዕድል እንደሚፈጥር ገልጸው ይህ ተግባር በቀጣይነትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.