የኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት ጉዞ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 12፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን የምታደርገውን ድርድር በስኬት ለማጠናቀቅ በርካታ ማሻሻያዎችና የድርድር ተግባራትን ስታከናውን ቆይታለች፡፡
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ ከ23 ዓመታት በላይ የወሰደውን የአባልነት ድርድር ባለንበት የፈረንጆቹ 2026 መጨረሻ ለማጠናቀቅ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል፡፡
ኢትዮጵያ በአባልነት ሂደቱ ዙሪያ ከተለያዩ ሀገራት ጋር ድርድር ስታደርግ የቆየች ሲሆን፤ በዛሬው ዕለትም ከዩናይትድ ኪንግደም የድርድር ቡድን ጋር የአባልነት የሁለትዮሽ የገበያ ዕድል ድርድር በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።
በውይይቱ ላይ የኢትዮጵያ የአባልነት ድርድር ሂደት አበይት ተግባራትን በተመለከተ ለድርድር ቡድኑ አባላት ገለጻ መደረጉን ተናግረዋል።
ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት ለኢትዮጵያ የአባልነት ሂደት ለሚያደርገው ድጋፍና ዘላቂ አጋርነት ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ኢትዮጵያ የልማት ፍላጎቷን ያገናዘበ ገንቢና መፍትሔ ተኮር የገበያ አቅርቦት ማቅረቧንና እስካሁን ከ11 ሀገራት ጋር ድርድር ማጠናቀቋን አብራርተዋል።
ለሁለት ቀናት በሚቆየው በዚህ መድረክ ከዩናይትድ ኪንግደም ጋር የሚደረገው ውይይት ስምምነቱን በይፋ ለመፈራረም የሚያስችል አዎንታዊ ውጤት እንደሚያስገኝ ይታመናል።
ይህም የኢትዮጵያን የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት ሂደት በእጅጉ እንደሚያፋጥን ነው የሚኒስቴሩ መረጃ ያመለክታል፡፡