Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ – ሀገረ መንግሥት የምትገነባ ሀገር

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሀገር መገንባት በአንድ ቀን የሚጠናቀቅ ሥራ ሳይሆን ትውልዶች የሚፈጽሙት ታላቅ ጉዞ ነው፤ ኢትዮጵያ ዛሬ በዚህ ጉዞ ውስጥ ትገኛለች።

የመደመር መንግሥት፣ ጊዜያዊ ስኬትን ብቻ ሳይሆን ለዘመናት የሚጸና ሀገረ-መንግሥት የመገንባት ራዕይ ይዞ ተነስቷል።

ይህ ራዕይ በሶስት ምሰሶዎች ላይ መልህቁን ጥሏል፤ የመጀመሪያው የጸና ሀገረ-መንግሥት ግንባታ ነው፡፡

በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ብዙ ፈተናዎች ባሉበት ሁኔታ እንኳ፤ ዜጎቿ በነቂስ ወጥተው ድምጻቸውን የሰጡበትን ነጻ፣ ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ ጠቅላላ ምርጫ በስኬት አጠናቅቃለች።

ምርጫ የዲሞክራሲያዊ ስርዓት ማጠናከሪያ ምሰሶ በመሆኑ ይህ ስኬት እንደ ቀላል የሚታይ አይደለም፡፡

ጠንካራ ሀገር የሚገነባው በጠንካራ ተቋማት ብቻ በመሆኑ፤ ምርጫ ቦርድ፣ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን፣ የፍትህና የፀጥታ ተቋማት እንደ አዲስ ተደራጅተው በስኬት ጎዳና ላይ ናቸው።

ሁለተኛው ምሰሶ፡ የማትበገር ሀገር መገንባት ነው፡፡ስርዓቶች ይቀያየራሉ፤ መንግስታት ያልፋሉ፤ ነገር ግን ተቋማት ሲጠነክሩ ሀገር ትቀጥላለች።

ኢትዮጵያ ዛሬ የምትገነባቸው ተቋማትና ሀሳቦች፣ ትውልዶች የሚዘክሯቸው፣ ሀገርን ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚያሻግሩ ናቸው።

ሦስተኛው የኢትዮጵያ የሀገረ መንግሥት ግንባታ ምሰሶ፡ የብልጽግና ተምሳሌትነት ነው፤መደመር መንግሥት የትናንትናውን ታሪካዊ ቅርስ እያደሰ፤ የዛሬውን ትውልድ እያነቃቃ፣ ነገንም እያሻገረ ይገኛል።

ይህ የትውልድ ተከታታይነት በንግግር ሳይሆን በተግባር እየተረጋገጠ ነው፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ ግን አንድ ጥልቅ እውነታ አለ፤ ይኸውም የኢትዮጵያ ሕዝቦች፣ ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ በጥልቅ የተሳሰረ ማንነት የሚጋሩ መሆናቸው ነው።

አንዳንዶች ይህን የጋራ ታሪክ በተቃራኒው አቅርበው የልዩነት ዘር ሲዘሩ ኖረዋል፤ እውነታው ግን ሌላ ነው፤ ይህ አብሮነት ከጥንት ጀምሮ የነበረ፣ የጋራ ሀገር የመገንባት ጥልቅ ፍላጎት ውጤት ነው።

አሁን እየተካሄደ ያለው ሀገራዊ የምክክር ሂደት የዘመናት የታሪክ ስብራቶችን ለመጠገን ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር እጅግ ወሳኝ ሚና እየተጫወተ ነው።

ይህ ሂደት በምንም መንገድ በግማሽ አይቆምም፤ ሀገረ መንግሥት መገንባት፣ ያልተቋረጠ ርብርብ፣ የላቀ ትኩረት፣ የጋራ ቁርጠኝነት የሚፈልግ ነው።

ይህ ደግሞ ኢትዮጵያን በእያንዳንዱ ርምጃዋ ታሪኳን እንድትፅፍ ጠንካራ፣ የማትበገር፣ ብልጽግናዋን የምታረጋግጥ ሀገር ያደርጋታል።

በአፈወርቅ ዓለሙ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.