ለጋራ ርዕይ የሚታትር የጋራ ግብ ያለው አመራር መፍጠር ተችሏል – አቶ አረጋ ከበደ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአማራ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የአሻጋሪ እድገትና የዘላቂ ልማት ዕቅዱን በባለቤትነት ይዞ የሚፈጽም፣ በጋራ ርዕይ ላይ የሚታትርና በዓላማ የተግባባ አመራር መፍጠር ተችሏል አሉ።
የክልሉ የ2018 በጀት ዓመት የአሻጋሪ እድገትና ዘላቂ የልማት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማና የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ መድረክ እየተካሄደ ይገኛል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ የተቋማትን የመፈጸም አቅም በማሳደግና የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በማላቅ አምራችና ተወዳዳሪ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ መገንባት ይገባል፡፡
የተጠናቀቀው የ2018 በጀት ዓመት በጋራ ትጋትና ጥረት የአሻጋሪ እድገትና ዘላቂ የልማት ዕቅዳችንን ከንድፈ ሃሳብ ባሻገር ተግባራዊ ውጤቶችን ያየንበት ዓመት ነበር ብለዋል።
እነዚህን ስኬቶች በማስቀጠልና የአፈጻጸም ችግሮችን በማረም ለ2019 በጀት ዓመት በጋራ መቆምና በዕቅድ ተመስርቶ መፈጸምን ባሕል ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።
“አርቆ ማየት አልቆ መሥራት” በሚል መሪ ሀሳብ እየተካሄደ በሚገኘው መድረክ ላይ የፓርቲና የመንግሥት የ2018 ዓ.ም እቅድ አፈፃፀም ሪፖርትና የ2019 ዓ.ም እቅድ ላይ ውይይት እንደሚደረግበት ተገልጿል።