ከበዓል ማድመቂያነት እስከ አዘቦት ባህል
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በሰው ተኮር የልማት አቅጣጫዋ ዜጎች በተለይም ሕፃናት፣ ተማሪዎች፣ አረጋውያንና በተለያዩ ምክንያቶች ድጋፍ የሚሹ ወገኖችን ኑሮ ለማሻሻል በርካታ ተግባራትን እያከናወነች ትገኛለች።
የመደመር መንግሥት ዘላቂ እድገትን ከዜጎች ዕለታዊ ሕይወት፣ ክብርና ማኅበራዊ ደህንነት ጋር ለማስተሳሰር ከሚያከናወናቸው ሰው ተኮር ሥራዎች መካከል የተማሪዎች ምገባ መርሐ ግብር እና የምገባ ማዕከላትን በማቋቋም አረጋውያንን የመመገብ ተግባራት ይጠቀሳሉ፡፡
እነዚህ ተግባራት ትናንት ለሀገራቸው የሰሩትን፤ ውለታ የዋሉትን ከማክበር ባለፈ ነገዋን የሚሰሩ ተማሪዎችን ከጉዟቸው እንዳይገቱ የሚያደርጉ ናቸው፤ የመደጋገፍ ባህልንም ያጠነክራሉ፡፡
በዓላትን በማስመልከት እጅ ላጠራቸው ዜጎች ማዕድ በማጋራት የተጀመረውን በጎ ተግባር ወደ ተቋማዊ አሰራር ከፍ በማድረግ በተማሪዎች ምገባ እንዲሁም የምገባ ማዕከላትን በማቋቋም ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡
በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተስፋ ብርሀን በሚል ስያሜ የምገባ ማዕከላት ተቋቁመው ለዜጎች የምገባ አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡
በእነዚህ ማዕከላት ራሳቸውን ለመመገብ አቅም ያነሳቸው አረጋውያን፣ አካል ጉዳተኞች፣ እንዲሁም የሀገር ባለውለታዎችና በየወረዳው በማህበራዊ ኮሚቴዎች የተመረጡ ዝቅተኛ ኑሮ ያላቸው ነዋሪዎች ተጠቃሚ መሆን ችለዋል፡፡
በከተማ አስተዳደሩ፣ በበጎ ባለሀብቶች እንዲሁም በተለያዩ ተቋማት ድጋፍ የሚንቀሳቀሱት እነዚህ ማዕከላት፤ ተደራሽነታቸው በየጊዜው እየተስፋፋ ይገኛል።
የተስፋ ብርሀን የምገባ ማዕከላት የምግብ እርዳታ መስጫ ብቻ ሳይሆኑ፤ የፍቅር፣ የሰብዓአዊነትና የህብረተሰብ አብሮነት መገለጫዎች ናቸው፡፡
በአጠቃላይ በመዲናዋ ለአቅመ ደካሞች በራቸውን ክፍት አድርገው የሚጠብቁ 30 የምገባ ማዕከላት ተከፍተው በየዕለቱ በርካታ ዜጎችን እያገለገሉ ይገኛሉ።
በእነዚህ የምገባ ማዕከላት ተጠቃሚ የሆኑ ዜጎችን ከተረጂነት ወደስራ እድል ተጠቃሚነት እንዲሸጋገሩ ማድረግ ደግሞ ሌላኛው አስደናቂ ጉዞ ነው፡፡
በዚህ ረገድ የከተማ አስተዳደሩ በቅርቡ የምገባ ማዕከላት ተጠቃሚ ለነበሩ 400 ነዋሪዎች መነሻ ካፒታልና የመስሪያ ቁሳቁስ አሟልቶ ወደ ሥራ እንዲገቡ አድርጓል፡፡
በእነዚህ የምገባ ማዕከላት ተመጋቢ የነበሩ ተጠቃሚዎችም በሂደት በምገባ አገልግሎት የሥራ እድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ ይህን የማዕድ ማጋራት መርሐ ግብር በየተቋማቱ እንዲሁም በማህበረሰቡ ውስጥ የሁሉም ልማድ ማድረግ ይገባል፡፡
ኢትዮጵያ ለራሷ የምታንስ ሀገር አይደለችም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የማዕድ ማጋራት ተግባርን ባህል ማድረግ ከተቻለ የብዙዎች ጓዳ እንደሚሞላ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በትዕግስት ግዛቸው