Fana: At a Speed of Life!

ቀጣዩ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል ስኬታማ እንዲሆን በቅንጅት እየተሠራ ነው – አፈ ጉባዔ ሰዓዳ አብዱረህማን

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) 21ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል በስኬት እንዲከበር በፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ በኦሮሚያ ክልልና በጅማ ከተማ አስተዳደር በቅንጅት እየተሠራ ነው አሉ የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባዔ ሰዓዳ አብዱረህማን።

በ21ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል ዝግጅት ዙሪያ በጅማ ከተማ የውይይት መድረክ ተካሂዷል።

በመድረኩ አፈ ጉባዔ ሰዓዳ አብዱረህማን ፥ በዓሉ በስኬት እንዲከበር ክልሉ ኃላፊነቱን ከተረከበበት ጊዜ ጀምሮ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች በትኩረትና በቅንጅት ሲከናወኑ ቆይተዋል ብለዋል።

በዓሉ የኢትዮጵያን ብዝሃነት፣ አብሮነት፣ የጋራ እሴቶችና የህዝቦችን መተሳሰር የሚያጎለብት ነው ሲሉ ተናግረዋል።

እንዲሁም 7ኛው ጠቅላላ ምርጫና ሀገራዊ ምክክር በሰላም በተጠናቀቁበት ማግስት የሚከበር በመሆኑ ከቀደሙት በዓላት ለየት ያደርገዋል ነው ያሉት።

አፈ ጉባዔዋ በዓሉ ለሀገረ-መንግሥት ግንባታ ተጨማሪ አቅም በሚፈጥር መልኩ እንዲከበር እየተሠራ መሆኑንም አመልክተዋል።

21ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በኦሮሚያ ክልል አዘጋጅነት፣ በፌዴሬሽን ምክር ቤት አስተባባሪነት በጅማ ከተማ ይከበራል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.