ሰማያዊ እና አረንጓዴ መለዮ ለባሾቹ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ኃይል ለአህጉረ አፍሪካና ለዓለም ሰላም ዋጋ እየከፈለ የሚገኝ የሰራዊት ክፍል ነው፡፡
ኢትዮጵያ ከ70 ዓመታት በላይ የዘለቀ እና በአፍሪካ ቀዳሚ የሆነ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ልምድ ያላት ሀገር ስትሆን ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ የሰላም ማስከበር ሚናዋን አሁንም አጠናክራ ቀጥላለች፡፡
ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ቀዳሚዎቹ የሰላም አስከባሪ ላኪ ሀገሮች አንዷ ናት። በኮሪያ፣ በኮንጎ፣ ላይቤሪያ፣ ሩዋንዳ፣ ቡሩንዲ፣ ሱዳን እንዲሁም በሶማሊያ ሰራዊቷን አሰማርታ አኩሪ ገድል መጻፏን ታሪኳ ያሳያል፡፡
አሁን ላይ ኢትዮጵያ በደቡብ ሱዳን፣ ሶማሊያ እና በሱዳን አቢዬ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰማያዊ መለዮ ለባሽ ሰራዊቶችን አሰማርታ የቀጣናውን ሰላም እያስጠበቀች ትገኛለች፡፡
በተለይም ኢትዮጵያ ለደቡብ ሱዳን ነጻነት እና ጸጥታ መረጋገጥ ትልቅ ሰብአዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ እና ወታደራዊ አስተዋጽኦ አድርጋለች።
ዛሬም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ስር ሕዝብን ለመጠበቅና ግጭትን ለመከላከል ከ1 ሺህ 300 በላይ ሰላም አስከባሪ የኢትዮጵያ ወታደሮች ደቡብ ሱዳን ይገኛሉ፡፡
እነዚህ ሰማያዊ መለዮ ለባሾች ውድ ህይወታቸውን በመገበር በአህጉሪቱ ሰላም እና መረጋጋት መስፈን አስተፅኦ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡
ኢትዮጵያ በሶማሊያ በሚካሄደው የአፍሪካ ህብረት የሰላም ማስከበር ተልዕኮ (አውሶም) ማዕቀፍ ውስጥ ሽብርተኝነትን በመዋጋት እና የሶማሊያን ሰላም በማስከበር ረገድ ሚናዋን እየተወጣች ትገኛለች፡፡
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድና በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣናዊ ሰላምን፣ ጸጥታን እና የኢኮኖሚ ትስስርን ለማረጋገጥ አሁንም በኢጋድ (IGAD) እና በአፍሪካ ኅብረት ማዕቀፎች አማካኝነት ሰላም የማስከበር እና የቀጣናው መሪነት ሚናዋን እየተወጣችም ነው፡፡
በሚኪያስ አየለ