Fana: At a Speed of Life!

ዘርፉን ያበዛው ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ኢኮኖሚዋን ለማሳደግ፣ የምርት አቅሟን ለማስፋት እና አዲስ የኢኮኖሚ ማዕከል ለመገንባት በተለያዩ ዘርፎች ሰፊ ስራዎችን ሰርታለች።
የእነዚህ ስራዎች ዋና ዓላማ ግብርና ላይ ብቻ ተመስርቶ የነበረውን ኢኮኖሚ ወደ ኢንዱስትሪ፣ አገልግሎት፣ ዲጂታል ኢኮኖሚና የውጭ ንግድን ታሳቢ ያደረገ ኢኮኖሚ ለመገንባት ሰፊ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡
ግብርና የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ መሰረት በመሆኑ በስንዴ፣ ቡና፣ ሆርቲካልቸር፣ ሰሊጥና ሌሎች የግብርና ምርቶች ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ ነው። በተለይም የበጋ መስኖ ስንዴ ምርት መስፋፋቱ ኢትዮጵያን ከስንዴ አስመጪ ሀገር ወደ ስንዴ ላኪ ሀገር ማሸጋገር አስችሏል፡፡
ሆኖም ይህን ግብርና መር ኢኮኖሚ ከላይ በተቀሱት ዘርፎች ለመደገፍ ባለፉት አመታት በትኩረት ሲሰራ ቆይቷል፡፡
የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ማስፋፋት፣ የማምረቻ ዘርፍን ማበረታታትና የውጭ ኢንቨስትመንትን መሳብ የማክሮ ኢኮኖሚ ለውጡ አንዱ አቅጣጫ ነው። ይህም ሀገሪቱ ጥሬ ዕቃ ብቻ ከመላክ ይልቅ እሴት ጨምራ ምርት እንድትልክ የሚያስችላትን መሰረት መገንባት ያስቻለ ነው።
የኮሪደር ልማት በከተሞች ውስጥ መንገድ፣ የእግረኛ መንገድ፣ አረንጓዴ ስፍራ፣ የመዝናኛ ቦታ፣ የንግድ ማዕከልና የመጓጓዣ መሠረተ ልማትን በተቀናጀ መልኩ ለማልማት ታስቦ ተከናውኗል። ይህም ከተሞችን የንግድና የኢንቨስትመንት ማዕከላት ለማድረግ የረዳ ስር ነቀል ለውጥ አምጥቷል፡፡
የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂን በመከተል የዲጂታል ክፍያ፣ የፋይናንስ ቴክኖሎጂ፣ ኢ-ኮሜርስ፣ የቴክኖሎጂ ስታርትአፕ እና ዲጂታል የመንግሥት አገልግሎቶች እንዲያድጉ ትኩረት ተሰጥቷል። ይህ ኢትዮጵያን በአፍሪካ የዲጂታል ኢኮኖሚ ተዋናይ ለማድረግ መልካም ጅማሮዎች ታይተዋል።
የኢኮኖሚ እድገት ከኃይል አቅርቦት ጋር በቀጥታ የተያያዘ በመሆኑ በውሃ፣ በፀሐይ፣ በንፋስና በሌሎች የንፁህ ኃይል ምንጮች ላይ ስራዎች ተጠናክረው ተሰርተዋል። የታላቁ የህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያን የኃይል አቅም ከማሳደግ ባሻገር የቀጣናውን የኃይል ገበያ ለማስፋፋት የሚያስችል ሀብት ለመሆን በቅቷል።
ኢትዮጵያ ያላትን ታሪካዊ፣ ባህላዊና ተፈጥሯዊ ሀብቶች ወደ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለመቀየር በቱሪዝም መሠረተ ልማትና መዳረሻዎች ላይ የተሰሩ ስራዎች ፍሬ ያፈሩ ናቸው። ይህ የውጭ ምንዛሪ ገቢን፣ የሥራ ዕድልንና ንግድን በማሳደግ ረገድ ከፍተኛ ተጠቃሚነትን አረጋግጧል፡፡
የባንክና የፋይናንስ ዘርፉን ማሻሻል፣ የውጭ ኢንቨስትመንት ተሳትፎን ማስፋፋትና የውጭ ምንዛሪ ገበያን ማሻሻል በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ርምጃ የተወሰደባቸው አበይት ጉዳዮች ናቸው፡፡ይህ የኢኮኖሚ ማሻሻያ የግሉ ዘርፍ በተሻለ ሁኔታ እንዲሳተፍና ኢኮኖሚው በገበያ መርሆች እንዲመራ ማድረግ አስችሏል።
ኢትዮጵያን ከውስጥ ገበያዎቿ ጋር እንዲሁም ከክልላዊና ከዓለም ገበያ ጋር ለማገናኘት የመንገድ፣ የባቡር፣ የአየር መጓጓዣና የሎጂስቲክስ አቅም ላይ ትኩረት ተደርጓል። ይህም የምርት መጓጓዣ ወጪን ለመቀነስና የንግድ ትስስርን ለማጠናከር ያገዘ ርምጃ ነው።
የአየር ትራንስፖርት ልማት፣ የአዲስ አበባን የንግድ ማዕከልነት ማጠናከርና ከአፍሪካ እና ከዓለም ገበያዎች ጋር ትስስርን ማስፋፋት ኢትዮጵያን የአፍሪካ የንግድ፣ የትራንስፖርትና የዲፕሎማሲ ማዕከል የማድረግ ርዕይ ውስጥ ይገኛል።
ባለፉት ስምንት ዓመታት የተሰሩት ስራዎች በአንድ ዘርፍ ብቻ የተገደቡ ሳይሆኑ ግብርናን ማዘመን፣ ኢንዱስትሪን ማስፋፋት፣ ዲጂታል ኢኮኖሚን መገንባት፣ ኢነርጂን ማሳደግ፣ ቱሪዝምን ማስፋፋት፣ ከተሞችን ማዘመን፣ የፋይናንስ ሥርዓትን ማሻሻልና የንግድ ትስስርን ማጠናከር ላይ ያተኮሩ ናቸው።
በዚህ መሠረት የኢትዮጵያ ራዕይ ብቻውን የኢኮኖሚ እድገት ሳይሆን ኢትዮጵያን በምርት፣ በንግድ፣ በቴክኖሎጂ፣ በፋይናንስና በቃጣናዊ ትስስር የምትመራ የአፍሪካ ኢኮኖሚ ማዕከል ለማድረግ ያለመ ነው።
በአቤል ነዋይ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.