Fana: At a Speed of Life!

የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን መከበር የሕዝቦችን ትስስር ለማጠናከር ዕድል ፈጥሯል – አፈጉባኤ አገኘሁ ተሻገር

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን መከበር የሕዝቦችን ትስስር ለማጠናከርና ቱባ ባህሎችና እሴቶች እንዲታወቁ ዕድል ፈጥሯል አሉ የፌዴሬሽን ም/ቤት አፈጉባኤ አገኘሁ ተሻገር፡፡

በጅማ ከተማ የሚከበረውን 21ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ለመመልከትና ለመገምገም የተዘጋጀ መድረክ እየተካሄደ ነው፡፡

አፈጉባኤው በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በዓሉ በጥንታዊቷና በታሪካዊ ውበቷ በምትታወቀው ጅማ ከተማ መከበሩ በርካታ ታሪካዊ እውነታዎችን ለማስተዋወቅና የሕዝቦችን የጋራ ታሪክ ለማጉላት ዕድል ይፈጥራል።

በዓሉ ሀገራዊ ምክክር በስኬት ከተጠናቀቀና 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በዲሞክራሲያዊ ሂደት ከተከናወነ በኋላ የሚከበር በመሆኑ ልዩ ትርጉም ይሰጠዋል ነው ያሉት፡፡

የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል በሕዝቦች መካከል አንድነትን፣ አብሮነትንና የጋራ እሴቶችን በማጠናከር ለሀገረ መንግሥት ግንባታ የሚያበረክተውን ሚና በሚያጎላ መንገድ ሊከበር እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

በዓሉ የሚከበርባቸው ከተሞች በልማት፣ በኢንቨስትመንትና በህዝቦች ትስስር እንዲጠናከሩ ምቹ አጋጣሚ መፍጠሩንም ተናግረዋል፡፡

በከተማ፣ በክልልና በፌዴራል ደረጃ ለተዘጋጀው የበዓሉ ረቂቅ ዕቅድና እስካሁን ለተከናወኑ ሥራዎች እውቅና በመስጠት፥ የተጀመሩት የዝግጅት ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ አቅጣጫ ሰጥተዋል፡፡

በአብዱረህማን መሀመድ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.