የትምህርት ማሻሻያው ፍሬዎች
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ዘመናዊና የበለፀገች ሀገርን ለመገንባት መሠረቱ የሰለጠነ፣ ችግር የመፍታት ክህሎት ያለውና መሪ ትውልድ ማፍራት መቻል ነው።
ለዚህ ደግሞ የትምህርት ስርዓት መዘመን አንድ ሀገር የሰለጠነ፣ መምራት፣ መፍጠንና መፍጠር የሚችል ትውልድን ለመቅረፅ ፥ ችግር የመፍታት ክህሎት ያለው ዜጋን ለማፍራት ሚናው የላቀ ነው ፡፡
ታላቁ ደራሲና ጋዜጠኛ የክብር ዶክተር ከበደ ሚካኤል “ጃፓን እንደምን ሰለጠነች?” በተሰኘው መጽሐፋቸው የጃፓንን የስልጣኔ ምስጢር ሲያብራሩ፤ ጃፓናውያን ከምንም ነገር አስቀድመው ለትምህርትና ለቴክኖሎጂ እውቀት የሰጡት ከፍተኛ ትኩረት ለዛሬው የስልጣኔ ማዕረግ እንዳበቃቸው ይጠቅሳሉ።
ኢትዮጵያም ይህንን እውነት በመገንዘብ ላለፉት ጥቂት ዓመታት በትምህርት ዘርፉ ላይ መሠረታዊ የፖሊሲ ማሻሻያዎችን ስታደርግ ቆይታለች። የማንኛውም አዲስ አሰራርና ለውጥ ጅምር እንደሚገጥመው ፈተና ሁሉ፣ የትምህርት ስርዓቱን ጥራት ለማስጠበቅ የተወሰደው እርምጃም መጀመሪያ ላይ በብዙዎች ዘንድ ስጋትንና ተቃውሞን አስነስቶ ነበር። ከዚህ ቀደም የነበረው ከፍተኛ የተማሪዎች ማለፍ ቁጥር በድንገት መቀነሱ ቢያስደነግጥም፣ መንግሥት ግን ከጊዜያዊ የቁጥር ብዛት ይልቅ ዘላቂ ለሆነው የትምህርት ጥራትና ብቃት ቅድሚያ በመስጠት ጉዞውን ቀጥሏል።
ይህ ቁርጠኝነት ባልተቋረጠ ሂደት ውስጥ ተስፋ ሰጪ ፍሬዎችን ማሳየት ጀምሯል። የትምህርት ሚኒስቴር መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፦ለአብነት በ2016 ዓ.ም፦ የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ከወሰዱ ተማሪዎች መካከል ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ያለፉት 5.4 በመቶ ብቻ ነበሩ፤በ2017 ዓ.ም ደግሞ የማለፊያ ውጤት ያመጡት ተማሪዎች ቁጥር ወደ 8.9 በመቶ አድጓል።
በዘንድሮ በ2018 ዓ.ም ይህ ቁጥር በከፍተኛ መሻሻል 12.8 በመቶ በመድረስ የረጅም ጊዜ ጥረት ውጤት መስጠት መጀመሩን አረጋግጧል።
ይህ ተስፋ ሰጪ እድገት ኢትዮጵያ በትምህርት ዘርፉ የያዘችው መሠረታዊ የማሻሻያ መስመር ትክክለኛ መሆኑን ያመላክታል። ጥራቱን የጠበቀ ትምህርት ለሀገሪቱ የምርምርና ፈጠራ አቅም መጎልበት፣ ለጠንካራ ዴሞክራሲያዊ ተቋማት ግንባታ እንዲሁም ለመልካም አስተዳደር መስፈን መሠረት ነው።
ሀገር በዓለም አቀፍ መድረክ ተወዳዳሪና ከፍ ያለች ሆና የምትቆመው በዕውቀት በተገነቡና በፈጠራ በመጠቁ ዜጎቿ በመሆኑ፣ ይህንን ብቁ ትውልድ የማፍራት ሂደት የስኬት ግብ ለማድረስ የመንግሥት፣ የወላጆች፣ የተጽዕኖ ፈጣሪዎችና የጠቅላላው ማህበረሰብ የተቀናጀ ትብብር ወሳኝነት አለው።
በቤተልሔም ግርማ