በምክክር የተሟሸው የመግባባት ዴሞክራሲ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሒደት ውስጥ ለረጅም ዓመታት ምላሽ ሳያገኙ የዘለቁ ጥያቄዎች መኖራቸው ግልጽ ነው፡፡ በተለይም ከፖለቲካ አካታችነት መጓደል ሳቢያ በርካቶች ሃሳባቸው እና ጥያቄያቸው ሳይደመጥ ቆይቷል፡፡
ይህም “ኢትዮጵያ ሁላችንም አላዳመጠችንም” የሚል ብሶት እና ቁጭትን መውለዱ አልቀረም፡፡
ለዚህ አብነትም ወደ ሀገራዊ ምክክሩ መክፈቻ ዕለት ወደ ኋላ እንመለስ፤ ሙዶ አኮን አስታወሳችኋት? ከደቡብ ኦሞ ዞን የካራ ማሕበረሰብ ተወካይ ሆና ምክክሩ ላይ የተሳተፈች ሴት ናት።
ሙዶ በቀጥታ ስርጭት ዓለም እየተመለከተው በነበረው የሀገራዊ ምክክር ድግስ እንዲህ አለች፡- “ለብዙ ዘመናት ታሪክን ከሩቅ ቆመን እንመለከት ነበር። ተናጋሪዎች እና ወሳኞች ሌሎች ነበሩ።
ዛሬ ግን ሀገሬ እንድናገር ጠርታኛለች።” በርግጥም ሀገራዊ ምክክሩ እንደሙዶ ሁሉ ሰሚ ብቻ የነበሩ በርካቶችን ተናጋሪ በማድረግ አዳምጧቸዋል። ለዘመናት የጠብና ቁርሾ ምክንያት የሆኑ ችግሮች እንዲፈቱ በር መክፈት ችሏል።
አለመግባባት አለመደማመጥ ፈተና ነው። ባለመግባባት መንገድ ብዙ ትውልዶች የገነቡት ተስፋ ለመፍረስ ከወር ያነሰ ጊዜ ሊበቃው ይችላል።
በኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ሰላም፣ ፖለቲካዊ መረጋጋት እና የጋራ ሀገራዊ እድገት ለመገንባት በሚደረገው ረዥም ጉዞ ውስጥ፣ ሀገራዊ የምክክር ሂደቱ ታሪካዊና ስልታዊ ምዕራፍ ሆኖ ተመዝግቧል።
በተለይም የዚህ ሂደት ስኬት፣ የመደመር መንግሥት አንግቦት የተነሳውን “የመግባባት ዴሞክራሲ” ፍልስፍና ከንድፈ ሀሳብ አልፎ በተግባር ያረጋገጠ ትልቅ ማሳያ ሆኗል። የመደመር አስተሳሰብ ዋነኛ ምሰሶ ሀገራዊ ጉዳዮችን በጋራ መግባባት፣ በጋራ ባለቤትነት እና በሰለጠነ የውይይት መንገድ መፍታት እንደሆነ በተደጋጋሚ ተረጋግጧል።
ታሪካዊው የምክክር ሂደት፣ የተወሰኑ የፖለቲካ ልሂቃን ብቻ የተደራደሩበትና የተስማሙበት ከላይ ወደ ታች የሚወርድ ውሳኔ አልነበረም። ይልቁንም በልሂቃን ብቻ ሳይሆን ከመላው ሀገሪቱ ማዕዘናት የመጡ አርሶ አደሮች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ወጣቶች፣ ሴቶች እና አጠቃላይ ማህበረሰቡ በቀጥታ የተሳተፉበት ህብር ድምጾች የሰሙበትና አካታች ሂደት ነበር።
ኖቤል ተሸላሚው አርተር ሊዊስ “ብዝሃ ማንነት ባላቸው ሀገራት ሁሉ ካልተደመጠ አደጋ ነው” ይላል። ለዚህም ባህላዊውና አሸናፊው ሁሉንም የሚወስድበት ፖለቲካ በተከፋፈሉና በርካታ ብሔረሰቦች ባሏቸው ሀገራት ውስጥ እሳት ላይ ነዳጅ እንደ መጨመር ጽንፈኝነትንና መገለልን ሲጋብዝ መኖሩን ዋቢ ያደርጋል።
የመደመር ፍልስፍና ግን “እኔ ሳልሸነፍ አንተም ሳትሸነፍ በጋራ ማሸነፍ እንችላለን” በሚል የጋራ እሴት ላይ የቆመ ነው። ይህ አስተሳሰብ እያንዳንዱ ዜጋ በሀገሩ ጉዳይ ላይ እኩል ድምፅና ባለቤትነት እንዲኖረው ያደርጋል፤ ማንም ዜጋ ከጠረጴዛው ውጭ እንዳይቀር በር ይከፍታል። እንደሙዶ አኮ አይነት ዜጎችም በሀገራቸው ጉዳይ ሰሚ ብቻ ሳይሆን ውሳኔ ሰጪና ተናጋሪ እንዲሆኑ ያደርጋል።
መደመር በሃይልና በጫና ከመሸናነፍ ይልቅ በስክነትና በምክክር የወል ትርክትን መፍጠርን ያስቀድማል፤ ያረጀ ቂምና ጥርጣሬ በምክክር እሳት እንዲቀልጥ የማድረግ መርህም አለው።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ለመግባባት ዲሞክራሲ መረጋገጥ ትልቅ ማሳያ ሆኖ በኢትዮጵያ አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል።
የታሪክ መዛግብት እንደሚያሳዩት፣ በሀገሪቱ ቀደም ሲል የተደረጉ በርካታ የፖለቲካ ሽግግሮች የጥቂት ልሂቃን ድራማና የይስሙላ ስምምነት በመሆናቸው ዘላቂ ሰላም ማምጣት አልቻሉም ነበር።
የአሁኑ ምክክር የቀየረው ይሄንን መንገድ ነው። በሂደቱ ከአራቱም የሀገሪቱ ማዕዘናት የተወጣጡ ዜጎችን፣ አርሶ አደሮችን፣ የእጅ ጥበብ ባለሙያዎችን፣ አባገዳዎችን፣ የሃይማኖት መሪዎችንና የሲቪክ ማህበራትን ድምፅ ከመንደር እስከ ዋና ከተማ ሰምቷል። ሴቶች፣ ወጣቶችና የአካል ጉዳተኞችም በውይይቱ ላይ የራሳቸውን ህመም፣ ፍላጎትና የመፍትሔ ሀሳብ በነፃነት አቅርበዋል።
እኒህ ዜጎች ከቀረቡት 400 አጀንዳዎች ውስጥ በ396 ያህሉ ተስማምተዋል። ይህም 99 በመቶ ማለት ነው።
የሀገራዊ የምክክር ሂደቱ ስኬታማ መሆን ለመግባባት ዲሞክራሲ መረጋገጥ በርካታ ዘላቂ ድሎችን የሚያስገኝ ነው። በህዝብና በመንግስት ተቋማት መካከል የታጣውን እምነት መልሶ በመገንባት ህጋዊነትን ያጠናክራል፤ የወደፊት የህግና የስርዓት ማሻሻያዎችም የብዙኃኑን ፍላጎት ያካተቱ እንዲሆኑ መንገድ ይጠርጋል። ከሁሉም በላይ ደግሞ የግጭት መንስኤዎችን ከስራቸው በመመርመርና በመፍታት ለልማት የሚመች ዘላቂ ሰላማዊ ሁኔታ ይፈጥራል።
በአፈወርቅ እያዩ