Fana: At a Speed of Life!

ሁልጊዜም ሕልማችን ትልቅ ሊሆን ይገባል – በ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ፈተና 590 ያመጣው ተማሪ ሮቤል ጌታቸው

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 22፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የምናልመው ነገር ትልቅ ከሆነ የሚመጣው ውጤትም ከፍተኛ ይሆናል አለ በ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ፈተና በተፈጥሮ ሳይንስ ዘርፍ 590 ያመጣው ተማሪ ሮቤል ጌታቸው፡፡
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሆሳዕና ከተማ የሊች ጎጎ አዳሪ ት/ቤት ተማሪ የሆነው ሮቤል ጌታቸው ÷ በ2018 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከፍተኛ ውጤት በማምጣቱ መደሰቱን ለፋና ዲጂታል ገልጿል፡፡
“ለ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ፈተና የተዘጋጀሁበት መንገድ ውጤታማ አድርጎኛል፤ ጥሩ ውጤት እንደማመጣም ጠብቄ ነበር” ይላል ተማሪ ሮቤል፡፡
ጥናት ላይ በሚሆንበት ሰዓት በትኩረት እንደሚያጠና የሚገልጸው ተማሪው÷ በጥናት ሰዓቱ ማስታወሻ የመያዝ እና ጥያቄዎችን የመስራት ልምድ እንዳለው አስረድቷል፡፡
ጥያቄዎችን መስራት እና ማስታወሻ መያዝ ለውጤታማነቱ እንደረዳው በመግለጽ፤ “የተሳሳትኩትን በቀጣይ ቀን በትኩረት እያየሁ ደጋግሜ በማጥናቴ ከፍተኛ ውጤት እንዳመጣ አግዞኛል” ብሏል፡፡
8ኛ ክፍል እንዳጠናቀቀ ወደ ሊች ጎጎ አዳሪ ትምህርት ቤት መግባቱን የሚናገረው ተማሪ ሮቤል÷ ወደ አዳሪ ትምህርት ቤቱ ለመግባት ፈተናውን በጥሩ ሁኔታ እንደሰራ ያስታውሳል፡፡
“አዳሪ ትምህርት ቤት ስትሆን ትኩረትህ በሙሉ ትምህርት ላይ ብቻ ይሆናል፤ ከትምህርት ውጪ ሌላ ነገር አይኖርም፤ ትኩረታችን በሙሉ ትምህርት ላይ በመሆኑም ውጤታማ ሆነናል” ብሏል፡፡
ከጓደኞቹ ጋር በጋራ እንደሚያጠና የሚናገረው ተማሪ ሮቤል÷ ትምህርት ቤቱ እና መምህራንም አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉላቸው ጠቁሟል፡፡
“እናት እና አባቴ መምህራን ናቸው፤ እነሱ በትምህርት ዘርፍ በመሆናቸው እኔም ትምህርት ላይ ትኩረት እንዳደርግ አድርጎኛል” ሲል ገልጾ÷ ወላጆቹ የሚያስፈልገውን ነገር እንደሚያሟሉለት፣ እንደሚጠይቁት፣ እንደሚከታተሉት እና እንደሚመክሩት ተናግሯል፡፡
ገና የ9ኛ ክፍል ተማሪ እያለ ከአራት ዓመት በፊት የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ የመልቀቂያ ፈተና ከ700 እንደነበር በመጥቀስ÷ በወቅቱ ከ700 ማምጣት የሚፈልገው 695 እንደነበር ያስታውሳል፡፡
“ከዝግጅት ባለፈ እሰራለሁ ብዬ አልም የነበረውን ውጤት ደብተሮቼ ላይ ሁሉ እጽፍ ነበር፤ ስናልም ሁላችንም ትልቅ ነገር ነው ማለም ያለብን” የሚለው ሮቤል÷ አውሮፕላን አብራሪ የመሆን ሕልም እንዳለው ተናግሯል፡፡
በአቪዬሽን ዘርፍ ጥሩ ቦታ መድረስ እንደሚፈልግ እና ከልጅነቱ ጀምሮ ሕልሙ ፓይለት መሆን እንደነበር አጽንኦት ሰጥቷል፡፡
በወንድማገኝ ጸጋዬ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.