ሕዝቡ ጽንፈኞችን ከመታገል ባሻገር በልማት ሥራ ንቁ ተሳትፎ እያደረገ ነው – አቶ አረጋ ከበደ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 25፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአማራ ክልል ሕዝብ ከመንግሥት ጎን በመሆን ጽንፈኞችን ከመታገል ባሻገር በልማት ንቁ ተሳትፎ እያደረገ ነው አሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ።
የ2018 በጀት ዓመት የፓርቲና የመንግሥት ሥራ አፈጻጸም እንዲሁም የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ ትውውቅ መድረክ የክልሉ አመራሮች በተገኙበት ተካሂዷል።
ርዕሰ መስተዳድር አረጋ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ የክልሉን ሰላምና ጸጥታን ለማስጠበቅና ልማትን ለማሳለጥ የሚደረጉ ቅንጅታዊ ጥረቶች ተጠናክረው ይቀጥላሉ።
ለዚህም በየደረጃው ያሉ አመራሮች ሕብረተሰቡን በማሳተፍ የላቀ ሚናቸውን ይበልጥ እንዲወጡ አሳስበዋል።
የክልሉ ሕዝብ ከመንግሥት ጎን ሆኖ ጽንፈኞችን በመዋጋት በልማትና በሌሎች ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በንቃት እየተሳተፈ መሆኑን አንስተዋል።
አመራሩ ሕዝብን በቁርጠኝነት በማገልገል በትብብር የተጀመሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎችን አጠናክሮ በማስቀጠል ከዳር ማድረስ አለበት ነው ያሉት፡፡
በቀጣይ የክልሉን ሕዝብ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ ከመቼውም ጊዜ በላይ በቅንጅት እንደሚሰራ አጽኖት ሰጥተዋል።