ኢትዮጵያ ከ1 ነጥብ 1 ሚሊየን በላይ ዓለም አቀፍ ስደተኞችን የልማት ተጠቃሚ እያደረገች ነው – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 25፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ከ1 ነጥብ 1 ሚሊየን በላይ ዓለም አቀፍ ስደተኞችን ተቀብላ መብትና ክብራቸውን በማስጠበቅ የልማት ተጠቃሚ እያደረገች ነው አሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ÷ የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች አገልግሎት በራስ ዐቅም ያከናወነውን ውጤታማ ተቋማዊ ሪፎርም መጎብኘታቸውን አንስተዋል፡፡
በዚህ ወቅትም የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች አገልግሎት በራስ ዐቅም ያከናወናቸው ተግባራት ኢትዮጵያ አሳታፊና አካታች ልማትን እያረጋገጠች ያለች ሀገር መሆኗን የሚያሳዩ ናቸው ብለዋል፡፡
ይህ ሪፎርም የሥራ ቦታን ከማሻሻል ባለፈ፣ የሥራ ባህልን፣ የአገልግሎት ጥራትንና ተቋማዊ ዐቅምን የሚያጎለብት ለውጥ እንደሆነ አውስተዋል፡፡
በዋና መሥሪያ ቤቱ፣ በ8 ክልሎች በሚገኙ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶችና በ25 መጠለያ ጣቢያዎች የተከናወነው ሥራ በራስ ዐቅም ተቋማዊ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ያሳየ ጥሩ ተሞክሮ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
የመደመር እሳቤ በሆነው የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር በአትክልትና ፍራፍሬ፣ በዶሮና እንስሳት እርባታ፣ በንብ ማነብና ሌሎች ዘርፎች የተጀመሩ ሥራዎች ተቋማዊ ሪፎርም የሚለካው በተሻለ የሥራ አካባቢ ብቻ ሳይሆን በሚፈጥረው ምርታማነትና ውጤት ጭምር መሆኑን ያሳያሉ ነው ያሉት።
ስደተኞቹ የዲጂታል መታወቂያ ተጠቃሚ መሆናቸው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተሳትፏቸውን እያሳደገ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል፡፡
በራስ ዐቅም የሚመጣ ለውጥ የተቋምን ዐቅም ያጎለብታል፤ ይህ ደግሞ የሀገርን ዐቅም ይገነባል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ÷ በስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ያየነው ስኬታማ ጉዞ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።