Fana: At a Speed of Life!

ነዋሪዎች የሰጡንን ሃላፊነት በሚገባ በመወጣት ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት ይሰራል – ከንቲባ አዳነች

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 25፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ሕዝብ የጣለብንን እምነት እና የሰጠንን ሃላፊነት በሚገባ በመወጣት ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት ይሰራል አሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፡፡

ለተከታታይ ሁለት ቀናት ስናካሂድ የቆየው የከተማ አስተዳደሩ የቀጣይ 5 ዓመታት ስትራቴጂክ እቅድና የ2019 በጀት ዓመት እቅድ ውይይት ተጠናቅቋል።

ከንቲባዋ በዚህ ወቅትም ÷ በውይይቱ እቅዶቹን ይበልጥ ተጨባጭ በማድረግና በቀጣይ አምስት ዓመታት አልቆ በመፈፀም ሕዝቡ የጣለብንን እምነትና የሰጠንን ሃላፊነት ሳንሸራርፍ ለመፈፀም እንሰራለን ብለዋል፡፡

በዚህም የአዲስ አበባን ሕዝብ ተጠቃሚ የሚያደርጉ እጅግ ጠቃሚ፣ ገንቢ፣ ተግባቦት እና ዝግጁነት መፈጠሩን አመልክተዋል፡፡

ከሀገራዊ ፖሊሲና ስትራቴጂያችን በመነሳት ሕዝቡ በድጋሚ ሲመርጠን የገባነውን ቃል ለመፈፀም እንደ አዲስ አበባ “አዲስ አበባን የብልፅግና ተምሳሌት” ለማድረግ የጀመርነውን ጉዞ ዋና ርዕያችን አድርገናል ነው ያሉት ።

ለእቅዱ ስኬት የሕዝብና መንግሥት ከድህነት የመውጣት ፍላጎት፣ በከተማዋ የተፈጠረው የስራ ትጋት፣ በታማኝነት ማገልገል፣ በየትኛውም አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ በፍጥነትና በጥራት የመፈፀም ልምድና በጀትን በመቆጠብ መጠቀም ትልቅ ስንቅ ናቸው ብለዋል።

በቀጣይ ተቋማዊ ብቃትን ማረጋገጥ የሚያስችሉ በአሰራር፣ በአደረጃጀት፣ የዘመነ ቴክኖሎጂ በሚጠቀም የላቀ አገልግሎት መስጠት፣ የተቀናጀ ጥራት ያለው ሰፊ መሰረት ልማት በፍጥነት መገንባት ላይ በትኩረት እንደሚሰራ ጠቁመዋል፡፡

ተደራሽነትና ጥራት እንዲሁም ፍትሃዊነትን በማረጋገጥ አልቆ መፈፀም፣ ዓለም አቀፍ ደረጃን ያሟላ የጤና አገልግሎት መስጠት፣ የጤና ቱሪዝም ማዕከል መሆን፣ የከተማዋን የቱሪዝም መዳረሻ ከተማነት ማረጋገጥና አዲስ አበባን ህፃናትን ለማሳደግ ምርጧ አፍሪካዊት ከተማ ማድረግ ላይ እንደሚሰራም ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም ለወጣቶች ተጠቃሚነት፣ የሴቶች ፖለቲካዊ ተሳትፎ እንዲሁም በኢኮኖሚና ማህበራዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ፣ የበጎ ፍቃድ ሥራዎችን ባህል በማድረግ ማህበራዊ ፍትህን ማንገስ እና የኮሪደርና ወንዝ ዳርቻ ልማትን ማጠናከር ላይ ትኩረት ይደረጋል ነው ያሉት፡፡

እንዲሁም ማህበራዊ ፍትሕን ማንገስ፣ አምራችነትን ማሳደግ፣ ተረጂነትን መቀነስ፣ የስራ እድልን በሰፊው መፍጠር፣ የከተማ ግብርና፣ የፍሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ ስርዓትን ማዘመን እና ከተማዋን ጽዱ፣ ውብ እና ለሁሉም የምትመች ከተማ ማድረግ የእቅዳችን ትኩረቶች ናቸው ሲሉ ገልጸዋል።

የእቅዱ ቅኝትም ስትራቴጂክ እይታ ያለው፣ ራዕያችንን ለማሳካት አቅዶ መተግበር፣ የተለጠጠ፣ አካታች፣ ፍትሃዊ እንዲሁም አሳታፊ እንዲሆን ማድረግ መሆኑን አብራርተዋል፡

መድረኩ አመራሩ በዋናነት እቅዱን በተሟላ ሁኔታ የተረዳ፣ ስትራቴጂክ አመራር የሚሰጥ፣ በአስተሳሰብ አንድነት የሚቆም፣ ከተለያየ የጥቅም ትስስር ነፃ የሆነ፣ ግልፅነትና ተጠያቂነትን የሚያሰፍንና የከተማዋን ራዕይና ግብ የተጋራ እንዲሆን በተለየ መንገድ የተኬደበነት መሆኑን አውስተዋል፡፡

ልማትን በመንግሥት ብቻ ማሳካት እንደማይቻል ጠቁመው÷ የከተማዋን ነዋሪዎች ግለሰቦችና ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ፣ የግሉን ዘርፍ በማበረታታት፣ በጊዜ የለንም መንፈስ 24/7 የመፈጸም ባህልን ይበልጥ አሳድጎ በመዲናዋ ለማሳካት የተወጠነውን ትልቅ ራዕይ ለመፈፀም በላቀ እንተጋለን ብለዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.