2018 ዓ.ም ሀገረ መንግሥትን ለማጽናትና ለዴሞክራሲ ግንባታ ጽኑ መሠረት የተጣለበት ዓመት ነው – የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት የተገባደደው 2018 ዓ.ም በኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥትን ለማጽናትና ለዴሞክራሲ ግንባታ ጽኑ መሠረት የተጣለበት ዓመት ነው አለ፡፡
የአገልግሎቱ ሚኒስትር ዴዔታ ከበደ ዴሲሳ በ2018 በጀት ዓመት የተመዘገቡ ግዙፍ ሀገራዊ ስኬቶችንና መጪዎቹን የጳጉሜን ቀናት አከባበር አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም ሀገረ መንግሥትን ከማጽናትና የግጭት መንስኤዎችን ከመቅረፍ አኳያ ሀገራዊ ምክክር የተካሄደው በዚሁ ዓመት መሆኑን አስታውሰዋል፡፡
በጠቅላላ ምርጫው ከ54 ሚሊየን በላይ መራጮች መሳተፋቸውን ገልጸው፤ 2018 ዓ.ም ለዴሞክራሲ ግንባታ ጽኑ መሠረት የተጣለበትና የኢትዮጵያ የማንሰራራት ጉዞ መጀመሩ የተረጋገጠበት ዓመት እንደነበር አስገንዝበዋል፡፡
ግዙፍ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ወደ ሥራ የገቡበትና የተጠናቀቁበት ስኬታማ ዓመት እንደነበር አብራርተዋል፡፡
ለአብነትም ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅ እንዲሁም የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ፣ የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካና ሌሎች ግዙፍ ፕሮጀክቶች ግንባታ መግባቱን ጠቅሰዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ 1 ነጥብ 5 ትሪሊየን ብር ገቢ መሰብሰቡን ጠቁመው፤ ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ67 በመቶ ብልጫ እንዳለው አስረድተዋል።
በተጨማሪም በበጀት ዓመቱ 10 ነጥብ 2 ቢሊየን ዶላር ከወጪ ንግድ ገቢ ማግኘት መቻሉን ነው የገለጹት፡፡
4 ነጥብ 4 ቢሊየን ዶላር ካፒታል ያስመዘገቡ አዳዲስ ኢንቨስተሮች ወደ ሥራ ገብተዋል ያሉት ሚኒስትር ዴዔታው፤ 13 ነጥብ 2 ቢሊየን ዶላር ካስመዘገቡ የውጭ ባለሃብቶች ጋር የኢንቨስትመንት የመግባቢያ ሰነድ መፈረሙን አንስተዋል።
በግብርናው ዘርፍ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጉዞ ትልቅ ስኬት መመዝገቡን ጠቅሰው፤ የአገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመን በተሰራው ሥራ ከ100 በላይ የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ማዕከላት ወደ ሥራ መግባታቸውንም አብራርተዋል።
በመልካም ፈቃዱ