የዛሬው እመርታችን የትናንት ቁርጠኝነታችን ፍሬ ነው – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን
አዲስ አበባ፣ጳጉሜን 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የዛሬው እመርታችን የትናንት ቁርጠኝነታችን ፍሬ ነው አሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ ÷ ዛሬ የኢትዮጵያን ማንሠራራት የሚያመላክተውን የጳጉሜን 1 የእመርታ ቀን አክብረናል ብለዋል።
በዚህ ወቅትም ኢትዮጵያ ከቆመችበት ከተነሣች እና ከተንቀሳቀሰች ቆይታለች፤ አሁን በሙሉ አቅሟ ወደ ላቀ ከፍታ እያንሠራራች ያለችበት ጊዜ ላይ እንገኛለን ሲሉም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በችግር ውስጥ ዕድልን፣ በጉድለት ውስጥ አቅምን፣ በተስፋ መቁረጥ ውስጥ ተስፋን ፈልጋ የማግኘት ታሪካዊ ጽናት እንዳላት አውስተዋል፡፡
የዛሬው እመርታችን የትናንት ቁርጠኝነታችን ፍሬ ነው፤ የነገው ከፍታችን ደግሞ የዛሬ ትጋታችን ውጤት ይሆናል ነው ያሉት።
በግብርና የምግብ ሉዓላዊነታችንን እያረጋገጥን፣ በኢንዱስትሪ ከሸማችነት ወደ አምራችነት እየተሸጋገረን፣ በማዕድን ዘርፍ የተፈጥሮ ፀጋችንን በዕሴት ጭማሪ ወደ ሀገራዊ ሀብት እየቀየርን እንገኛለን ብለዋል።
በዲጂታል ለውጥና የአገልግሎት አሠራር ዘመናዊነትም ጠንካራ የኢኮኖሚ መሠረት ጥለናል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ÷ይህ ጉዞ ከጥገኝነት ወደ ራስን መቻል የሚያሸጋግር የኢትዮጵያ የእመርታ ጉዞ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
ለእኛ አምራችነት ዕሳቤም፣ ስልትም፣ ግብም ነው፤ ሥራችን፣ ንግግራችን እና ፕሮጀክቶቻችን ሁሉ ዕሴት የሚጨምሩና ምርት የሚያስገኙ መሆን እንዳለባቸው አብራርተዋል፡፡
ዛሬ ያገኘነውን እመርታ ወደ ነገ ከፍታ ለመቀየር የበለጠ መሥራት፣ የበለጠ ማምረት፣ የበለጠ መፍጠር እና መፍጠን ይጠበቅብናል ፤ በወጣቶቻችን እውቀት፣ በአምራቾቻችን ቁርጠኝነት እና በሕዝባችን አቅም ራሷን የቻለችና የማትበገር ኢትዮጵያን እንገነባለን ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ ማንሠራራት ይቀጥላል፤ እመርታው ይፋጠናል፤ የኢትዮጵያ ከፍታ አይቀርም ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡