የፌደራል ፖሊስ – በጽናት ሀገርን የማጽናት ገድል
አዲስ አበባ፣ጳጉሜን 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ያካሄደው ስር ነቀል ተቋማዊ ሪፎርም ለሀገሪቱ ዘላቂ ሰላምና ሉዓላዊነት ጠንካራ መሠረት መጣል ችሏል፡፡
በመደመር መንግሥት የጸጥታ ተቋማት የሪፎርም ማዕቀፍ የተተገበረው የፖሊስ ሪፎርም የደህንነትና የሕግ ማስከበር ተቋማትን በማዘመን የሕዝብን አደራና የሀገርን ሕልውና ማስጠበቅ ችሏል፡፡
በዚህም የፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ጥራትን በማሳደግ፣ የሳይበርና የድንበር ተሻጋሪ ወንጀል ስጋቶችን በከፍተኛ ደረጃ በመቀነስ በአፍሪካ ግንባር ቀደም የሕግ ማስከበር ተቋም ለመሆን በቅቷል።
ተቋማዊ ሪፎርሙ የፌደራል ፖሊስን ከፖለቲካ ነፃ በማድረግ ሕዝባዊነቱን ማጎልበት አስችሏል፡፡
በዚህም መሠረት የፌደራል ፖሊስ አሠራር በኅብረተሰብ አቀፍ መርህ ላይ እንዲገነባ ተደርጓል፤ ይህም ኅብረተሰቡን በፖሊስ ተቋማት ላይ ያለውን እምነት አጠናክሯል፡፡
በተጨማሪም የፖሊስ ሰራዊት አባላትን ከሁሉም የኢትዮጵያ ብሔሮችና ብሔረሰቦች እንዲሁም ከሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች ስብጥር ለማካተት ያስቻለ አሳታፊ የምልመላ ስርዓት በመዘርጋት የሀገራዊ አንድነትና የሀገር ፍቅር ማሳያ ሆኗል።
የፌደራል ፖሊስ በቴክኖሎጂ ዘመናዊነት በመታጠቅ ረገድም ከፍተኛ ርምጃ የተራመደ ሲሆን፤ የወንጀል መከላከል አቅሙን በከፍተኛ ሁኔታ አሳድጓል፡፡
በሰው ሰራሽ አስተውሎትና ሰው አልባ ድሮኖች በመታገዝ እንዲሁም ሕብረተሰቡን በከፍተኛ ሁኔታ ለማሳተፍ የሚያስችሉ የሕዝብ ጥቆማ መቀበያ መተግበሪያና ነጻ የስልክ መስመር ተግባራዊ በማድረግ ሰላምን ለማጽናት በትጋት እያገለገለ ይገኛል።
በተጨማሪም በሀገር ውስጥ የዲኤንኤና የሳይበር ወንጀል ምርመራዎችን ለማካሄድ የሚያስችል የፎረንሲክ ምርመራና የምርምር የልህቀት ማዕከል መገንባቱ፤ ተቋማዊ ነፃነቱንና ምርመራዎችን በሀገር ውስጥ የማካሄድ አቅሙን አረጋግጧል።
የሀገሪቱን ኢኮኖሚና ሕዝባዊ ደህንነት ለማስጠበቅ በተከናወኑ የተቀናጁ ኦፕሬሽኖች፤ ከ2013 እስከ 2017 ባሉት ዓመታት ውስጥ ከ53 ቢሊየን ብር በላይ ግምት ያለው ሕገወጥ የኮንትሮባንድ ንግድና እቃዎችን መቆጣጠር ተችሏል።
እንደ ልዩ የፀረ-ሽብር ኮማንዶና የኤምባሲዎች ጥበቃ መርሐ ግብር ያሉ ልዩ የሰራዊቱ ክፍሎች ሀገራዊ ደህንነትን እያስጠበቁ ይገኛሉ፡፡
ከኢንተርፖልና ከምስራቅ አፍሪካ የፖሊስ አዛዦች ህብረት ጋር በመተባበር የድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን በመከላከል ረገድም አኩሪ ተግባራትን እየፈጸመ የሚገኝ ጠንካራ የፖሊስ ተቋም ነው፡፡
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የሙያ ብቃት፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር፣ የሰብዓዊ መብቶች መከበርና የሀገር ፍቅር ስሜትን በማቀናጀት የኢትዮጵያን ተቋማዊ ፅናትና ዘመናዊነት በተግባር እያረጋገጠ የዘለቀ ሕዝባዊ ሰራዊት ነው፡፡
በአብረሃም አበራ