ፕሬዚዳንት ታዬ የኳታር ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጥሪ አቀረቡ
አዲስ አበባ፣ጳጉሜን 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ የኳታር ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች እንዲሳተፉ ጥሪ አቀረቡ።
ፕሬዚዳንቱ በተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች ዱባይ እየተካሄደ ካለው ዓመታዊው ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ጉባኤ ጎን ለጎን የኳታር ቻምበር የቦርድ አባል አሊ ቢን አብዱላቲፍ አል ሚስናድ ጋር ተወያይተዋል።
ውይይቱ የኳታር ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በተለይም በግብርና፣ በጤና፣ በመሠረተ ልማት ግንባታ፣ በማማከር አገልግሎትና በሌሎች የኢንቨስትመንት አማራጮች ተሳትፏቸውን ማሳደግ በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጓል።
ፕሬዚዳንት ታዬ በወቅቱ በኢትዮጵያ የውጭ ባለሀብቶችን ለመሳብና ምቹ የኢንቨስትመንት ከባቢ ለመፍጠር መንግሥት ትኩረት አድርጎ የሚሠራቸውን ሥራዎች አብራርተዋል።
በዚህም የኳታር ባለሀብቶች በሃገሪቱ ያሉትን ምቹና አስቻይ የኢንቨስትመንት አማራጮች እንዲጠቀሙና ግንኙነታቸው ይበልጥ እንዲጠናከር ጥሪ አድርገዋል።
የኳታር ቻምበር የቦርድ አባል አሊ ቢን አብዱላቲፍ አል ሚስናድም በበኩላቸው የኳታር ባለሀብቶች በግብርና፣ በጤና፣ በመሠረተ ልማት ግንባታ በተለይም በቤቶች ግንባታና በዲጂታል ልማት ዘርፍ ለመሳተፍ ፍላጎት አላቸው ማለታአቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በኢትዮጵያ ያለውን ምቹ የኢንቨስትመንት ከባቢ የኳታር ባለሀብቶች እንዲጠቀሙበት ለማድረግና በሁለቱ ሃገራት መካከል ያለውን የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር እንደሚሠሩም ተናግረዋል።