Fana: At a Speed of Life!

በዓልን ተከትሎ የፍጆታ አቅርቦት እጥረትና የዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል – የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል

አዲስ አበባ፣ጳጉሜን 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በዓልን ተከትሎ የፍጆታ አቅርቦት እጥረትና የዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል አለ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ንግድና ኢንቨስትመንት ቢሮ፡፡
የቢሮው ኃላፊ ታሪኩ አካሉ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት፤ የ2019 አዲስ ዓመት በዓልን የዋጋ ጭማሪ እና የአቅርቦት እጥረት እንዳይከሰት ሰፊ የገበያ ማረጋጋት እና የቁጥጥር ስራ ተከናውኗል፡፡
ለበዓል ፍጆታ የሚውሉ እንደ ምግብ ዘይት፣ ስኳር፣ ሽንኩርት፣ ጤፍ፣ የእርድ እንስሳት እና የእንስሳት ተዋጽኦዎችን ከአምራቾችና ከአስመጪዎች ጋር በትስስር በመስራት በበቂ ሁኔታ ወደ ገበያዎች እንዲቀርቡ መደረጉን ገልጸዋል፡፡
ዋጋ በሚጨምሩ ደላሎች ላይ ቁጥጥር ከመደረጉም ባሻገር፤ ምርቶች ከገጠር ወደ ከተማ በሚጓጓዙበት ወቅት የሚገጥሟቸውን ህገ ወጥ ኬላዎችና መስተጓጎሎች የማስቀረት ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
የበዓል ግብይትን አጋጣሚ በመጠቀም ያለአግባብ ዋጋ በሚጨምሩ፣ ምርት በሚደብቁ እና ህገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴ በሚያደርጉ አካላት ላይ ጥብቅ ርምጃ እንደሚወሰድም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ከንግድና ኢንቨስትመንት ሴክተር እንዲሁም ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የተወጣጣ ግብረ ኃይል በገበያ ቦታዎችና በንግድ ድርጅቶች ተሰማርቶ ጥብቅ ቁጥጥር በማድረግ ላይ እንደሚገኝም አመልክተዋል፡፡
ማህበረሰቡ ግብይት በሚፈጸምበት ወቅት ያልተገባ የዋጋ ጭማሪና ምርት የመደበቅ አዝማሚያ ሲያስተውል በአቅራቢያ ለሚገኙ የንግድና የጸጥታ አካላት ጥቆማ በመስጠት ትብብር እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በመልካም ፈቃዱ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.